ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሚያዝያ 8/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ የተመዘገቡ የለውጥ ውጤቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የፓርኮቹ ምርታማነት፣ የባለሀብቶች ቁጥር እና የኤክስፖርት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን “በየሉዓላዊነት ልብ” ቆይታ ገልፀዋል።

ቀደም ሲል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የነበረው የባለሀብቶች ቁጥር 36 ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጥር አድጎ ከ300 በላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በዘርፉ የተፈጠረው የሥራ ዕድል ከ27 ሺህ ወደ 90 ሺህ በላይ ከፍ ያለ ሲሆን፣ የሼዶች የመያዝ አቅምም ከ45 በመቶ ወደ 88 ማደጉን ማደጉን አብራርተዋል።

በተለይም በለውጡ ወቅት ሥራ የጀመሩት ጥቂት ፓርኮች ብቻ የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ላይ አብዛኛዎቹ ፓርኮች ወደ ሙሉ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።

በኤክስፖርት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችንም የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ቀደም ሲል ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኝ የነበረው 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በሚቀጥለው ዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይደርረል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ሌላው ጉልህ ለውጥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት 60 ፐርሰንት የሚሆኑት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተያዙ መሆናቸውንና ይህም ከለውጡ በፊት ከነበረው የሁለት ሰዎች ተሳትፎ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን እና ወደ ነጻ ንግድ ቀጠና የመቀየር ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፣ ለዚህም በድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና የታየው የ27 ሚሊዮን ዶላር የንግድ ሽያጭ ስኬታማ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ሽግግር አምራችነትን ከንግድ እና ከሎጅስቲክስ ጋር በማሳለጥ የሀገር ውስጥ ምርትን ለመተካት እና የሸቀጦችን ዋጋ ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ ሎጅስቲክስ ቁልፍ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ኤርፖርት ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የንጹህ ኢነርጂ አቅርቦት እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመቀነስ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

በሚካኤል ኅሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review