AMN- ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረና በታሪካዊ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ ጠንካራ መሠረት ያለው ሲሆን፣ በንጉሠ ነገሥታት ዘመን ከነበረው መንፈሳዊና ባህላዊ ትስስር ጀምሮ በሶቪየት ሕብረት ዘመን እስከነበረው የርዕዮተ-ዓለምና የጦር መሣሪያ ድጋፍ፣ እንዲሁም በዘመናዊው የጂኦፖለቲካ ምህዳር ወደ አዲስ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሯል።
የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እ.ኤ.አ በ1898 የተጀመረ ሲሆን፣ ሩሲያ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ያደረገችው የህክምናና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለዚህ ግንኙነት መሠረት መሆኑንም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በቅርብ ጊዜያትም ኢትዮጵያ በምዕራባውያን አገራት ማዕቀብና ጫናዎች ለምሳሌ በትግራዩ ግጭት ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሲደቀኑባት፣ ሩሲያ በቪቶ ሥልጣኗና በድምጽ ተአቅቦ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እንዳይገባባት የማገጃ ሚና ተጫውታለች፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 2024 በይፋ የብሪክስ (BRICS) አባል እንድትሆን ሩሲያ በወቅቱ የቡድኑ ሊቀመንበር በመሆን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድጋፍ አድርጋለች።
በሌላ በኩል የሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂና የደህንነት ትብብር ከፍተኛ እምርታ እያሳየ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከሩሲያው የመንግሥት የኑክሌር ኮርፖሬሽን (Rosatom) ጋር በጋራ የኑክሌር ቴክኖሎጂ ማዕከልና የኃይል ማመንጫ ለመገንባት ስምምነት ላይ የደረሰች ሲሆን፣ ይህም በግብርና፣ በሕክምናና በኃይል አቅርቦት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

በየዓመቱ የሚካሄደው የጋራ የንግድ፣ ኢኮኖሚ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በካፒታል ኢንቨስትመንት ላይ ተጨባጭ ዕቅዶችን በመንደፍ ላይ ነው።
ከሶቪየት ሕብረት ዘመን ጀምሮ የነበረውን የወታደራዊ ትብብር በዘመናዊ መልክ በማደስ የጦር መሣሪያ አቅርቦት፣ የጥገና አገልግሎት፣ የመከላከያ ቴክኖሎጂ ሽግግርና በሩሲያ ወታደራዊ አካዳሚዎች ከፍተኛ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የሩሲያ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን በሳይንስ፣ ሕክምናና ኢንጂነሪንግ የሚሰጠውን የነፃ ትምህርት ዕድል እያሳደገው ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እና በሩሲያው ‘Roscosmos’ መካከል በጠፈር ምርምርና ሳተላይት ቴክኖሎጂ የጋራ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በታሪካዊ ወዳጅነት ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ አሁን ባለው የብዙ-ወገን የዓለም ሥርዓት ውስጥ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን መሠረት ያደረገ እመርታ እያሳየ ይገኛል።
በአስማረ መኮንን