
AMN- ጳጉሜን 5/2018 ዓ.ም
በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶ የሚቆጠሩ ታራሚዎችን መንግሥት በምሕረት እንዲፈቱ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ደ/ር) አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ገደ መልካም መሆኑን በምክክሩ ብቻ ሳይሆን በውጤቱም እያሳየ ነውም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም፤ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶ የሚቆጠሩ ታራሚዎችን መንግሥት በምሕረት እንዲፈቱ ማድረጉን አብስረዋል፡፡
መንግስት ይሄንን ያደረገበት ዓላማ የመጀመሪያው የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም ለመጀመር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ወደ ሀገራዊ ምክክር የመጡ ልዩ ልዩ ወገኖች በአንድም በሌላም የታሠሩ ወገኖች በይቅርታ እና በህግ አግባብ እንዲፈቱ ጠይቀው እንደነበርም ጠቁመው መንግሥት ይሄንን ተቀብሎ በሂደቱ ተስማምቶ ፈትቷል ብለዋል።
የምክክሩም ዓላማ ኢትዮጵያውያን በጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ የተግባቡባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲያቀርቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥትም ለምክክሩ ሐሳቦች ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ የይቅርታ ሂደት ማሳየት ጀምሯል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በዚህ የይቅርታ ሂደት የተፈቱ ወገኖች በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይታመናል።
ካለፈው መንገድ በመማር የወደፊቱን መንገድ የሰላምና የዴሞክራሲ መንገድ ያደርጉታል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማኅበረሰቡም እነዚህ ወገኖች በሀገር ሰላምና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ማገዝና መምከር አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አክለውም፤ ግጭትና ጦርነት አዋጪ አይደለም፤ የብዕርና የሐሳብ ጊዜ እንጂ የጠመንጃ እና የጉልበት ጊዜ አልፏል ሲሉም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ካሁን በኋላ የጠመንጃና የጉልበት ታሪክን አይመዘግብም፤ በታሪካችን ውስጥ በቂ ግጭቶችና ጦርነቶች መኖራቸውን የዘመን መጽሐፋችን አሳይቶናል፤ቀጣዩ ምእራፍ አዳዲስ መንዶችን እንጂ አሮጌ አካሄዶችን አይመዘግብምም ብለዋል።