AMN – ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ አስራ ሁለት የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች እና አራት የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ስርዓት ባትሪዎችን መረከቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም እያላበሳት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከሩሲያ መንግስት ጋር በደረስነው ስምምነት መሰረት፣ ዛሬ የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ አራት የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ስርዓት ባትሪዎችን ትረከባለች ሲሉ ጠቅሰዋል።
ወዳጄ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከስምምነታችን አንድ ዓመት አስቀድሞ እነዚህን የጦር አውሮፕላኖች እንድንረከብ ስላሳዩት ትጋት ላመሰግናቸው እወዳለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እነዚህን የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ሆናለች ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ወደፊትም የጋራ ደህንነታችንን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት እንድንቀጥል ትልቅ አቅም ይሆነናል ሲሉም ገልጸዋል።