AMN-ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ቀጣና የኃይል ሚዛኑን መሰረታዊ በሆነ መልኩ የሚቀይር ወታደራዊ ትጥቅ ዛሬ ተረክባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ይፋ እንዳደረጉት ኢትዮጵያ ከሩሲያ መንግሥት ጋር በደረሰችው ስምምነት መሰረት የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት የሱ-35 የጦር ጄቶች የተረከበች ሲሆን አራት የኤስ-400 የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን ትረከባለች።
ይህ የኢትዮጵያን የመከላከል አቅም ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ ደረጃ ያሸጋግረዋል። ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም እያላበሳት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ የተረከበቻቸው የሱ-35 የጦር ጄቶች በ4ኛ++ ትውልድ የሚመደቡና የአምስተኛ ትውልድ ቴክኖሎጂን የተላበሱ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች ናቸው።
አውሮፕላኑ የተገጠመለት “Irbis-E” ራዳር እስከ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ የጠላት ዒላማዎችን አስቀድሞ የመለየት፣ በአንድ ጊዜ 30 የአየር ላይ ዒላማዎችን የመከታተልና 8ቱን በአንድ ጊዜ የመምታት አቅም አለው።
በሰዓት እስከ 2ሺህ 400 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት የሚበረው ይህ ጄት፣ ያለ ነዳጅ መሙያ እስከ 3 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ ይገለጻል። ኢትዮጵያ እነዚህን ጄቶች በመታጠቅ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ መሆኗ፣ ማንኛውንም ስጋት በእንጭጩ የመቅጨትና ፍጹም የሆነ የአየር ላይ የበላይነትን ያጎናጽፋታል።
አስራ ሁለቱ የሱ-35 ጄቶች ከአራቱ የኤስ-400 ባትሪዎች ጋር ሲቀናጁ የኢትዮጵያን የአየር ክልል የማይደፈር ያደርገዋል። እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ብሔራዊ የልማት ተቋማቷን፣ የኢኮኖሚ አውታሮቿንና አጠቃላይ ዳር ድንበሯን ከማንኛውም የአየር ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ያስችላታል።

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ያደረጉት የጄቶችና የአየር መከላከያ ባትሪዎች ርክክብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማይነቃነቅ ዐለት ላይ ያጸናል። በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ የሚስተዋለውን የኃይል ፉክክር ለመመከትም ጠንካራ አቅም ይሆናታል።
ኢትዮጵያ ያላት ወታደራዊ የበላይነት በቀጣናው ሊፈጠሩ የሚችሉ የውክልና ጦርነቶችንና ነውጦችን በማስቀረት፣ ለጋራ ደህንነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት ድርሻው የጎላ ነው።
በታደሰ ሽፈራው