ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄት ባለቤት ሆናለች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄት ባለቤት ሆናለች

AMN-ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በመከላከያ ዘርፎች በአፍሪካ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

በመከላከያ ሰራዊቷ ግንባታ ረገድ አየር ኃይሏን በማዘመን ሀገራዊ ደህንነትን ማስጠበቅ የቻለች ሲሆን አሁንም የራሷን የመከላከል አቅም በብዙ መልኩ በመገንባት ለቀጣዩ ትውልድ የጸናች ሀገርን ለማስተላለፍ ያላት ቁርጠኝነት ተጠናክሮ መቀጠሉን የዛሬው እለት ስኬት አመላካች ሆኗል።

ኢትዮጵያ ትልቅና ታሪካዊ እንዲሁም ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር እንደ መሆኗ መጠን፤ ሉዓላዊነቷንና ደህንነቷን ለማረጋገጥ እንዲሁም የሀገሪቱን የመከላከያ አቅም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማጠናከር የምታደርገውን ጉዞ በሚገባ በሚያሳድግ መልኩ አዳዲስ የጦር ጄቶችን እና የአየር መከላከያ ስርዓቶችን ከሩሲያ ተረክባለች።

በዛሬው ዕለት በተከናወነው ታሪካዊ ስነ-ስርዓት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የመጀመሪያ የሆነውን የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች ተረክባለች ፡፡ ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገሪቱን የአየር ክልል በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክር፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን እና ጥቃቶችን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችል ነው።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የተሻለና የዘመነ ቴክኖሎጂ መታጠቅ የቻለች ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ትልቅ ምዕራፍም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤

በቂ ዝግጅት ያላቸው ሀገራት በቀላሉ አይደፈሩም:: መዘጋጀት ውጊያን ያስቀራል፤ ውጊያን ማስቀረት የሚፈልግ ማንኛውም ኃይል ደግሞ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አክለውም ይህንን አቅም በቀጣይነት በመገንባት የኮራች፣ የጸናች፣ ለልጆቿ የምትተላለፍ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለማኖር እንደ መሰረት መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review