AMN- ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም
በትግራይ ክልል በተዋረድ በሚዋቀሩ የሕዝብ አስተዳደር ተግባራት፣ የህብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የሚያሳልጥ አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑን በክልሉ የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር አስታወቀ።
ህገወጡ የሕወሓት ቡድን “እኔ ካልመራሁት” በሚል ርዕዮተ ዓለም በትግራይ ሕዝብ ስም እየነገደ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱ ይታወሳል።
ቡድኑ በየደረጃው የነበሩ የመንግሥት ተቋማትን በማፍረስ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ በማድረጉ ሕዝቡ ለከፍተኛ እንግልትና ለስነ ልቦናዊ ጉዳት ተጋልጦ ነበር።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ፤ በክልሉ ሰላም እንዲጸና፣ የሕዝቡ ሥነ ልቦና እንዲስተካከል፣ እንዲሁም ወደ ልማትና መልሶ ግንባታ ሥራዎች ለመግባት የሚያስችል ዝግጁነት እንዲኖር ለማድረግ በየደረጃው የሕዝብ መድረኮችን ማዘጋጀትና ለቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና አካታች ሁኔታዎችን መፍጠርን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን እንዲያከናውን የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
የባለአደራ አስተዳደሩ የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተዋረድ በሚዋቀሩ የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ የሕዝብ አስተዳደር ተግባራት አማካኝነት ሕዝባዊ አገልግሎቶችን ማሳለጥ የሚያስችል አደረጃጀት እየተፈጠረ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም አካባቢያዊና ሕዝባዊ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎችን የማቋቋም እንዲሁም የሕዝብ ውይይቶችን የማካሄድ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህ እንቅስቃሴ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት ትልቅ አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና አስፈጻሚው አያይዘውም፣ በአብዛኛዎቹ የትግራይ አካባቢዎች ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታችኛውን የመንግሥት መዋቅር በጊዜያዊነት የሚያስተዳድሩ አመራሮች በመምረጥ የፈረሱ መዋቅሮችን መልሶ የመዘርጋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በቀሩት አካባቢዎች በሕዝብ የነቃ ተሳትፎ፣ ፍጹም ዴሞክራሲና ግልጽነት ባለው አሠራር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደሚከበር አረጋግጠዋል።
ባለአደራ አስተዳደሩ ሲቋቋም ከሕዝብና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሰጡትን ኃላፊነቶች በስድስት ወራት ውስጥ ውጤታማ ማድረግ እንደ ታለመ የገለጹት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ለዚህም ሰላምን ለማጽናት ከሕዝብ ጋር መምከር እና የፈረሱ መዋቅሮችን በድጋሚ መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር እና ለቀጣዩ ምርጫ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ባለአደራ አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ዋና አስፈጻሚው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡