የተፈጥሮና የልማት ቅንጅት- የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እርምጃዎችና ተጨባጭ ውጤቶች

You are currently viewing የተፈጥሮና የልማት ቅንጅት- የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እርምጃዎችና ተጨባጭ ውጤቶች

AMN- ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በስፋት ተግባራዊ ስታደርግ የቆየችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ስትራቴጂ፣ ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን በጽናት እንድትቋቋም እና የከባቢ አየር ብክለትን በዘላቂነት እንድትከላከል ያስቻለ የልማት ስልት ነው፡፡

ይህ ታላቅ እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ወደፊት በሙሉ ኃይሏ የምትተገብረውን ከካርበን ነፃ የሆነ የበለጸገ ኢኮኖሚ ከአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ጋር የተሳሰረ እንዲሆን መሠረት ጥሏል።

በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ የተያያዘችው አረንጓዴ አሻራ አካሄድ ከተፈጥሮ ጥበቃ ባለፈ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘላቂነት ያለው ሚና በተጨባጭ ማስረጃዎች የተደገፈ ሁለገብ ውጤቶች ተገኝተውበታል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መተከላቸው የደን ሽፋንን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያስቻለ ሲሆን፣ ይህም የአፈር መሸርሸርን ከመቀነስ ባለፈ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጎለብትና የድርቅ አደጋ የመቋቋም አቅም እንዲጎለብት አድርጓል።

በተጨማሪም የታዳሽ ኃይል ምንጮች መስፋፋት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ አዳማ እና የሌሎችም የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ሀገሪቱ ከነዳጅ ጥገኝነት ወጥታ ንጹሕ ኃይል እንድትጠቀምና የካርበን ልቀትን በከፍተኛ ደረጃ እንድትቀንስ እያደረጓት ይገኛሉ።

በሌላ በኩል የከባቢ አየር ብክለትን ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎች፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች የሚካሄደው የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ ስፍራዎች ግንባታ የከተሞችን የአየር ጥራት እንዲሻሻል እና የአካባቢ ጽዳት እንዲጠበቅ አድርጓል።

በተለይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ለመቀነስና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀምን ለማስፋፋት የተወሰደው የፖሊሲ እርምጃ በከተሞች የሚለቀቀውን የመኪና ጭስና የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን በመቀነስ ረገድ ፈጣንና አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

ይህም የከተማ አየር ብክለትን በመከላከል የሕዝብን ጤና ለማረጋገጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እርምጃ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ከመቀነስ ባለፈ የአከባቢ አየር ብክለትን በውጤታማነት ለመከላከል የሚያስችል ዘላቂ ስትራቴጂ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

አረንጓዴ አሻራን ፣ የታዳሽ ኃይል ልማትን እና ንጹሕ ትራንስፖርት አጠቃቀምን ያስተሳሰረው ይህ አካሄድ፣ ሀገሪቱ እየገነባች ላለችው የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ልማት መሠረት በመጣል ለአካባቢ ጥበቃና ለዘላቂ ልማት አርአያ የሚሆን የልማት መስመር ሆኗል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review