AMN – ኅዳር 6/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ፣ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት እና የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በኦማን፣ ሙስካት እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የበይነ-ሃይማኖት እና የባህል ከፍተኛ መሪዎች የትግበራ ዕቅድ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ከኅዳር 6 እስከ ኅዳር 8 ቀን 2019 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ይህ ዓለም አቀፍ መድረክ፤ በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋና ጉዳት እያስከተለ የመጣውን የጥላቻ ንግግር ለመግታት በሚረዱ አሠራሮች፣ እንዲሁም ግጭትን በተቀናጀ መንገድ በመከላከል አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት የሃይማኖት መሪዎች በሚኖራቸው ጉልህ ሚና ላይ ምክክር የሚደረግበትና ዓለም አቀፍ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው።
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የጉባኤው ልዑካን ያላቸውን የካበተ ልምድ፣ ጥበብ እና ዕውቀት ለተሳታፊዎች እንደሚያካፍሉ ይጠበቃል። በተያያዘም በጉባኤው ከሚሳተፉ የተለያዩ ሀገራት የሃይማኖት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር ምክክር በማድረግ፣ የተጀመሩትን ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚደረግ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።