ሙስናን መታገልና ማስወገድ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው

You are currently viewing ሙስናን መታገልና ማስወገድ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው

AMN – ኅዳር 18/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ስነ- ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓለም ለ23ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ22ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ-ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ሙስና የሀገርን ሀብት ከማባከኑም በላይ የሕግ የበላይነትን፣ የፍትሕ ሥርዓትንና የሕዝብን እምነት የሚሸረሽር አደገኛ ወንጀል በመሆኑ የሃይማኖት አባቶች በቁርጠኝነት ሊታገሉት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሙስናን ለመከላከል የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ በመሆኑ ሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸውን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ሙስና በተደራጀ መንገድ የህዝብን ሃብትና ንብረት በመመዝበር፤ ፍትህ በማጓደል የሀገርን እድገትና ብልጽግና የሚገታ አስከፊ ችግር መሆኑን አመላክተው፣ መሰል የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ማህበረሰብን ማንቃትና ሙስና ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚያዊ እድገትና የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንቅፋት በመሆኑ በየዘርፉ ያለውን ብልሹ አሠራር ለመቅረፍ የሃይማኖት ተቋማት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የሃይማኖት አባቶች በትብብርና በተግባር በመሥራት የሙስና ወንጀሎችን ሰንሰለት ለመበጠስ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሙስናን ለመከላከል ሃይማኖታዊ አስተምህሮአቸውን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አበክረው እንደሚሰሩ የገለፁት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ የሀይማኖት አባቶች ናቸው ።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review