
AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም
የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የፀሃይ ብርሃንን በመጠቀም በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት እንዳይቋረጥ የሚያስችል አማራጭ ቴክኖሎጂ በወረዳ ጽ/ቤቶች በሙከራ ማስጀመሩን አስታውቋል፡፡

የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እያደረግ ባለው የተቋም ግንባታ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ ቴክኖሎጂ ማሸጋገሩን አስታውሷል፡፡
የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በሚገጥምበት ወቅት አገልግሎት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ በህብረተሰቡ በስፋት የሚነሳ ቅሬታ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ምንም እንኳን 2/3 በሚሆኑት የተቋሙ የወረዳ ጽ/ቤቶች የጄኔሬተር አቅርቦት ቢኖርም ከአዋጭነት እና ከቀጣይነት አኳያ ክፍተት ያለው መሆኑ ታይቷል ነው የተባለው።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ አማራጭ ታዳሽ የፀሃይ ብርሃን ሃይል ተጠቅሞ አገልግሎት በወረዳዎች እንዳይቋረጥ ማድረግ የሚያስችል ሙከራ ከፍተኛ የተገልጋይ ፍሰት ካለባቸው ወረዳዎች አንዱ በሆነው የቦሌ ወረዳ 12 ጽ/ቤት ዛሬ ተግባራዊ ተደርጓል።
በድምሩ 18 ፓናል ገጠማ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን እስከ 20ሺ KW ሃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም ተፈጥሮለታል።
ኤጀንሲው የፀሃይ ሃይልን በመጠቀም አገልግሎት ሳይቋረጥ መስጠት የሚያስችለውን የሶላር ቴክኖሎጂ ከኮርነር ስቶን ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚባል የአሜሪካ ድርጅት በድጋፍ የተገኘ መሆኑን የኤጀንሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቢ.አይ.ዜድ.ኢቲ. ፒ ኤል ሲ ስራውን በማስተባበር የሙከራ ትገበራው ዛሬ መከናወኑ ተመላክቷል።
በዕለቱ መርሃ-ግብር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ፣ የቦሌ ክ/ከተማ ዋና ስራ-አስፈፃሚ ወ/ሮ አለምፀሃይ ሽፈራው እንዲሁም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ የማነ ደሳለኝ ተገኝተዋል።
አቶ ዮናስ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኤጀንሲው በህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ችግሮች ለይቶ አንድም ሳይቀር ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የሃይል አማራጭ ስራውን በሁሉም ክ/ከተሞች የተመረጡ ወረዳዎች ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ታዳሽ ሃይልን የመጠቀም አማራጮችን በመከተል አዲስ አባባን ስማርት የማድረግ ውጥኗን ማሳካት የሚቻለው በእንዲህ ዓይነት አማራጮች እንደሆነም አንስተዋል።