ኢትዮጵያና አዘርባጃን ለጋራ ልማትና ብልጽግና ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

You are currently viewing ኢትዮጵያና አዘርባጃን ለጋራ ልማትና ብልጽግና ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

AMN ሐምሌ 21/2018

ኢትዮጵያና አዘርባጃን በተለያዩ ዘርፎች ለጋራ ልማትና ብልጽግና ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከአዘርባጃን ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ እና ልዑካን ቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹት፤ የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

አፈ-ጉባኤው ለአዘርባጃን ልዑካን ቡድን ስለ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠሯንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችንና አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ሥራዎችን ከማከናወኗ ባሻገር አልሚዎችን የሚደግፍ ፖሊሲ ቀርጻ እየተገበረች እንደሚገኝ የጠቀሱት አፈ ጉባኤው፤ ሀገሪቱ በግብርና፣ በማዕድንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ስኬታማ ሀገራዊ ምርጫ ማካሄዷንና አገራዊ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ገለልተኛ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ምክክር ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በተለያዩ መስኮች ለጋራ ብልጽግና ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የአዘርባጃን ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት በአዘርባጃን ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

አዘርባጃን በትምህርት፣ በአቅም ግንባታና በግብርና ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በትምህርት ዕድል ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈረም ጠቁመዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የሚያጸና መሆኑን ጠቅሰው፤ አዘርባጃን ለዚህ ስኬት በቁርጠኝነት እንደምትሠራና ከተለያዩ የትብብር መስኮች በተጨማሪ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review