ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የሦስት ሀገራት አምባሳደሮችን አሰናበቱ

You are currently viewing ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የሦስት ሀገራት አምባሳደሮችን አሰናበቱ

AMN ሐምሌ 21/2018

የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የሦስት ሀገራት አምባሳደሮችን አሰናበቱ።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ፣ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክርቲንሰን እና የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አሰናብተዋል።

አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሁለገብ ግንኙነቶችና ትብብርን ለማጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ፕሬዝዳንቱ ምሥጋና አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ አምባሳደሮቹ ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው የቆየ አጋርነት ላሳዩት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ለቀጣይ ሥራዎቻቸውም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በታላቅ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ናት።

በኢትዮጵያ በቆዩበት የሦስት ዓመታት የሥራ ዘመን በርካታ ውድ የሆኑ ተሞክሮ የቀሰምኩበት ነው ያሉት አምባሳደሯ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ሚናዋን በአግባቡ እየተወጣች መሆኑን አድንቀዋል።

ፊንላንድ እና ኢትዮጵያ በተለይም በትምህርት፣ በገጠር የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በግብርና እና በዲጂታል የመሬት ምዝገባ ዘርፎች የቆየ ትብብር እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ዘመናዊ እና ፈጣን ሽግግር አድንቀው፤ ይህም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በፈጠራ፣ በስታርት አፕ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኢንቨትምነት ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት የፊላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵየ እንዲሰማሩ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ እንደ ኖኪያ እና ቫይሳላ ያሉት ኩባንያዎችን በማሳያነት አንስተዋል።

የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክርስቲንሰን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በቆይታቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ምሥጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ኖርዌይ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በደን ልማት ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል።

የአረንጓዴ አሻራ፣ የደን ጥበቃ ሥራዎችና በኢትዮጵያ ኑሮን ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራትን ኖርዌይ መደገፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ፤ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያን ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት በማስታወስ፤ በጉብኝቱ ወቅት ከተደረሱት ስምምነቶች መካከል ብዙዎቹ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን እያሰፉ ሲሄድ፣ ተጨማሪ የህንድ ኢንቨስትመንቶች ወደ አገሪቷ እንደሚመጡም እምነታቸውን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review