AMN – ጥር 13/2017 ዓ.ም
በተለያየ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ከ625 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የእቅድ አፈፃፀም የስትሪንግ ኮሚቴ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደገለፁት የኢትዮጵያ ታምርት ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በተለያየ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ከ625 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል።
የአምራች ኢንዲስትሪዎች የማምረት አጠቃቀም አርባ ስድስት በመቶ የነበረ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መላኩ ንቅናቄው ከተጀመረ አንስቶ እስከ አሁን ያለንበት ደረጃ በአማካይ የማምረት አጠቃቀም ወደ ስልሳ አንድ በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡
ንቅናቄው ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከላይ እስከታች ያለው የመንግስት የበላይ አመራሩን ትኩረት እንዲያገኝና በዘርፉ ችግሮች ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ውይይት በማድረግ ለችግሮቹ የመፍትሔ ባለቤት በመሆን በጋራ መስራት በመቻሉ የማምረት አቅም አጠቃቀም፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት፣ በራስ ምርት የመኩራትና የመጠቀም ባህላችን እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በውይይት መርሃ ግብሩ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈፃፀም እየቀረበ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።