
AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ተወዳዳሪ የሆነች አለም አቀፍ ከተማ መገንባታችንን አጠናክረን ቀጥለናል ብለዋል ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ዛሬ በመንግስት እና ግል አጋርነት መርሀ ግብር ከአያት አክሲዮን ማህበር ጋር በመተባበር የ13,752 ቤቶች ግንባታን አስጀምረናል ብለዋል::
በካዛንቺስ አካባቢ ከኦቪድ ግሩፕ ጋር ካስጀመርነው ጋር ከ15 ሺሕ በላይ ቤቶችን የምናለማ ሲሆን ቅድሚያ የማልማት መብታቸውን በመጠቀም የሚገነቡ የግል አልሚዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 20 ሺሕ ቤቶችን የሚገነቡ መሆኑንም አመልክተዋል::

በከተማችን ያረጁ እና ለመኖር ምቹ ያልሆኑ እንደ ካዛንቺስ ያሉ አካባቢዎችን መልሰን ስናለማ በዋነኛነት የህዝቡን ዋንኛ አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነውን የመኖሪያ ቤትን ለመመለስ ሲሆን የመኖሪያ ቤቶችን ስንሰራ ቤት ብቻ ሳይሆን ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢዎችን እንገነባለንም ብለዋል::
ካሳንችስ ከመልሶ ማልት በፊት ነባር 8000 መኖሪያና ንግድ ቤቶች በጥቅሉ ወደ 21ሺ ነዋሪዎችን የሚገለገሉበት አካባቢ የነበረ ሲሆን በመልሶ ማልማት ስራችን 2 ሺሕ የንግድ ሱቆች እና ሀያ ሺሕ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ከ100 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች የሚገለገሉበት አካባቢ ይሆናልም ነው ያሉት ከንቲባዋ።
ካዛንቺስ ላይ የምንገነባው ይህ የካዛንቺስ አያት መንደር በውስጡ ማህበራዊ ግልጋሎትን የሚሰጡ ተቋማት ጨምሮ የመማሪያ ቦታዎች፣ የጤና ተቋማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ አረንጏዴ ቦታዎች፣ ሞሎች፣ ሱቆች እንዲሁም ሰፋፊ የመኪና ማቆሚያዎችን ያካተተ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል::
በሚቀጥሉት 18 ወራት ጊዜ ውስጥ የ15 ሺህ ቤቶች ግንባታን ለማጠናቀቅ ያቀድን ሲሆን ሁላችንም ለፕሮጀክቱ ስኬት በጋራ እንድንሰራ አደራ እያልኩ ንጹህ፣ ፅዱ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ተወዳዳሪ የሆነች አለም አቀፍ ከተማ መገንባታችንን አሁንም አጠናክረን ቀጥለናልም ነው ያሉት ከንቲባዋ በመልእክታቸው::

All reactions:
2727