AMN-መጋቢት 1/2017 ዓ.ም
መንግሥት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።
ሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማይናማር በእገታ ሥር ቆይተው ወደ ታይላንድ ከተሻገሩ 133 ኢትዮጵያውያን መካከል 32ቱ ዛሬ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገ ሲሆን፣ 43 ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዛሬ ምሽት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቀሪዎቹን በታይላንድ ማቆያ የሚገኙ 58 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ኤምባሲው ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተያያዘ መንግሥት ጃፓን በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ታይላንድ በማሻገር ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።
መንግሥት በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ሕብረተሰቡ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሀሰተኛ ቅስቀሳ ተታሎ የሥራ ስምሪት ውል ወደ አልተፈጸመባቸው ሀገራት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ አሳስቧል።