AMN- ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

የማንችስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ በዝውውር መስኮቱ ቀሪ ቀናት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማምጣት እንደሚጥሩ ተናግሯል።
ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስ እና ዩሪ ቲሊሞንስን ብዙም ሳይንዛንዛ በፍጥነት ማስፈረሙ ደጋፊዎች ተጨማሪ ተጫዋቾች በተመሳሳይ መልኩ ይመጣሉ የሚል ተስፋ ነበራቸው።
ነገር ግን ሁለቱ አማካዮች ኦልድትራፎርድ ከደረሱ ሳምንታት አልፈዋል። ቡድኑን የሚያጠናክሩ ተጫዋቾች ቢያስፈልጉም ዩናይትድ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ጊዜውን እየወሰደ ነው።
ማይክል ካሪክም ከዝውውር ጋር በተያያዘ ለቀረበለት ጥያቄ “ለቁጥር ብቻ ብለን አናስፈርምም ፤ ነገር ግን ቡድኑን የሚያሻስሉ ተጫዋቾች ያስፈልጉናል ፤ በዚህ ላይም እየሰራን እንገኛለን” በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
ዩናይትድ ከአንድሬ ሳንቶስ እና ዩሪ ቲሊሞንስ በተጨማሪ ወጣቱን የመስመር ተጫዋች ተይናን ቶምፕሰን እና አንጋፋውን ግብ ጠባቂ ካርል ዳርሎውን አስፈርሟል።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሚሳተፈው ዩናይትድ ቢያንስ አንድ አማካይ እና ለሉክ ሾው አጋዥ የሚሆን የግራ መስመር ተከላካይ እንደሚያስፈልገው ይነገራል። እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ማይክል ካሪክም በተወሰነ መልኩ ይህን ይጋራል።
“ አንድ ሁለት መሻሻል ያሉባቸው ቦታዎች አሉ ፤ አሁን ካለን በላይ የሚያሻሽል ስናገኝ ወደ ተግባር መግባታችን አይቀርም” ሲል ተናግሯል።
ካሪክ ከቀናት በኋላ በሚጀምረው አዲሱ የውድድር ዘመን ላይ የተሻለ ተፎካካሪ ለመሆን መዘጋጀታቸውንም ተናግሯል።
“ የገዘፈ ግምት ማስቀመጥ አልፈልግም ፤ ነገር ግን ያለፈውን የውድድር ዓመት ካጠናቀቅንበት መንገድ መነሻ ዘንድሮም ጥሩ ስራ መስራት እንችላለን” ብሏል።