“የድጋፍ ስርዓታችንን እናሻሽል!” በሚል መሪ ቃል የዓለም የአእምሮ እድገት ውስንነት (Down syndrome) ቀንን ከዲቦራ ፋውንዴሽን ጋር ማክበራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ግን ጌጥ መሆኑን በመገንዘብ፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትን በመደገፍ እና ለማህበረሰባችን በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ዲቦራ ፋውንዴሽን በአእምሮ እድገት ውስንነት የተጠቁ ልጆችን ከተደበቁት አዉጥቶ ፍቅርና እንክብካቤ እንዲያገኙ እንዲሁም የመማር እና የመታከም መብታቸዉ እንዲጠበቅ በማድረጉ ታላቅ ምስጋና ይገባዋልም ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች።
“በዚህ ዙሪያ የምትሰሩ አካላትን በሙሉ አቅሞቻችንን ሁሉ አሰባስበን በቅንጅት እንድንሰራ በመጠየቅ፣ የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት ለምትሰሩት አኩሪ ስራ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
በጤና ተቋማት በአእምሮ እድገት ውስንነት ለተጠቁ ህጻናት ነፃ የህክምና አገልግሎት የሚሠጥ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ በዚሁ ዘርፍ ለተሰማሩ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ እና ተማሪዎችም በተማሩበት የሙያ ዘርፍ የስራ እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች አረጋግጠዋል።