ኔዘርላንድስ ጎረቤቷ ቤልጂየም ንፋስ እየሰረቀችኝ ነው ስትል ክስ አቅርባለች፡፡
ቤልጂየም ሀገራቱን በሚያወስነው የሰሜን ባህር አቅራቢያ የተከለቻቸው የንፋስ ኃይል ማመንጫ ማማዎች ከኔዘርላንድስ ንፋስ እየሞጨለፉ መሆኑን የሀገሪቱ የዓየር ትንበያ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሬምኮ ቨርዚልበርግ፣ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎቹ ያሉበትን የቦታ አቀማመጥ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም “በሀገራችን ላይ ጠንካራ የንፋስ ስርቆት እየፈጸሙ ነው” ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ቤልጂየም በኔዘርላንድስ አቅጣጫ ከሚገኙ ተመሳሳይ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች እስከ 3 በመቶ የንፋስ ኃይል በማስኮብለል ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
“ወደ እኛ የኃይል ማዕከል የሚመጣው የንፋስ ፍጥነት እና ጉልበት መቀነሱን በልኬት አረጋግጠናል” ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በቀጣይ የንፋስ ስርቆቱን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራቱ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ቤልጂየም ንፋስ ሰርቀሻል መባሏን ተከትሎ እስካሁን የሰጠችው ምላሽ አለመኖሩንም ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
በኢዮብ መንግስቱ