
AMN-ግንቦት 23/2017 ዓ.ም
በመዲናዋ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 378 ስፍራዎች ልየታ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
ከ ኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፤ በከተማ አስተዳደሩ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን ልየታ በማድረግ በዘላቂነት ስጋቱን ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎች አብዛኛዎቹ በክረምት ጊዜ ለሚፈጠሩ ተፋሰሶች አመችነት የሌላቸውና ለጎርፍ ተጋላጭ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ በዘላቂነት የጎርፍ ተጋላጭነትን የሚቀንስ ስራ መሰራቱንም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል በንቅናቄ የጎርፍ ተፋሰስ ትቦዎችን የማፅዳት ስራዎች እንዲሁም ችግሮች ቢፈጠሩ አደጋን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ የጎርፍ ተፋሰሶች እና ቱቦዎች ላይ ቆሻሻ ከመጣል ሊቆጠብ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአልማዝ ሙሉጌታ