ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ
የጎደለውን እየሞላን ለውጥን አጠናክሮ ማስቀጠል የጋራ ዕዳችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ1984 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ባሉ 15 ዓመታት ውስጥ ለዓለም ገበያ ምርቶቿን በመላክ ያገኘችው አጠቃላይ ገቢ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ፡፡
በአንፃሩ ዘንድሮ በአንድ አመት ብቻ ለዓለም ገበያ ካቀረበችው ምርቶቿ ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ አግኝታለች፡፡ ይህን በአግባቡ ማስተዋል ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን በቁጭት መንፈስ ሠርቶ ለመለወጥ ዝግጁ መሆንን የሚጠይቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በነዚህ ዓመታት ለውጭ ከተላኩ ምርቶች መካከል የቡና እና ወርቅ ምርትን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ቡና ከ1984 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ባሉት 15 ዓመታት ውስጥ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሲሆን የተገኘው ዘንድሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ አስገኝቷል ፡፡ ይህ በብዙ ትጋት የተገኘ መሆኑን ጠቁመው በተለይም የአረንዴ አሻራ ሥራ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
በ15 ዓመት ውስጥ ለውጭ ከተላከ የወርቅ ምርት 508 ሚሊየን ዶላር ገቢ ነበር የተገኘው፡፡ በአንፃሩ በዘንድሮ ዓመት በ6 እጥፍ በማደግ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡
በአንድ ዓመት ብቻ የተመዘገበው ውጤት በተከታታይ አራት እና አምስት ዓመታት ማስመዝገብ ከተቻለ ውጤቱን መገመት ቀላል ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከፍተኛ ሁኔታ የሚዳሰስ ለውጥ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
የጎደለውን እየሞላን ለውጥን አጠናክሮ ማስቀጠል የጋራ ዕዳችን ነው ያሉ ሲሆን ሳንደክም የሚመጣ ውጤት ባለመኖሩ መጨከን እና ዋጋ መክፈል አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበቱ ከ30 በመቶ በላይ የነበረው ወደ 13 ነጥብ 5 በመቶ መውረዱንም አስገንዝበዋል፡፡
ልማት ባለበት ሀገር የዋጋ ግሽበት ተንቀሳቃሽ ፈተና በመሆኑ ይህን ሊከላከል የሚችል ጠንካራ ሥራ እየሠሩ መቀጠል ግን ወሳኝነት ያለው ነው ብለዋል፡፡