የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የሚሳካው በየደረጃው ያሉ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን አካላት ጉዳዩን በባለቤትነት ሲመሩ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የሚሳካው በየደረጃው ያሉ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን አካላት ጉዳዩን በባለቤትነት ሲመሩ መሆኑ ተገለጸ

AMN- ግንቦት 29/2017 ዓ.ም

ጽዱ እና ምቹ ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስረከብ ጉዞው የሚሳካው በየደረጃው ያሉ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን አካላት ጉዳዩን በጥልቀት ተገንዝበው ለማኅበረሰብ በማስረዳት እና ሥራዎችን በባለቤትነት ሲመሩ መሆኑ ተገልጿል።

የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል “ጽዱ ኢትዮጵያ” በሚል መጠሪያ ሁለተኛው ሀገራዊ ንቅናቄ ተጀምሯል።

ንቅናቄዉ በአካባቢ ጥበቃ ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን በመፍጠር ለመጪው ትውልድ ሀለንተናዊ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጥረት አካል መሆኑ ተመላክቷል።

የንቅናቄው ማስጀመሪያ አካል የሆነው የሚዲያ አካላት ሚናን የሚመለከት የፓናል ውይይት በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል።

በፓናል ውይይቱ የተሳተፉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ “የአካባቢ ጥበቃ ከሀገርም አልፎ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ስለሆነ በአጀንዳ የተመራ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ እንደሚያስፈልግ” ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ትርጕም ባለው መልኩ ማሳደጉንም አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።

በከተሞች የተጀመሩ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማቶችም ጽዱ እና ንጹሕ አካባቢ የመፍጠሩ አካል መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ከእንጦጦ ጀምሮ የአዲስ አበባ ወንዞችን በማልማት እና በማከም አጠቃላይ የከተማዋን ተፋሰሶች የማጽዳት ተጨባጭ እንቅስቃሴ መጀመሩም ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የከተማ ኮሪደር ልማቱ ወደ ተለያዩ ከተሞች ተስፋፍቶ የፍሳሽ ሥርዐቱን በማሻሻል፣ ጽዱ የመናፈሻ ቦታዎችን በመፍጠር፣ ለኑሮ ምቹ ያልኾኑ አካባቢዎችን ገጽታ በመቀየር ጽዱ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ጥረቱን ከፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ይዞ በመጠቀም ንጹሕ አካባቢ መፍጠር እና ንጹሕና ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጅ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ባለመሆኑ ማኅበረሰቡ ባህል እስኪያደርገው ድረስ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽኑ አጀንዳ አድርጎና ባለቤት ኾኖ እንዲሠራበት አሳስበዋል፡፡

የኪነ ጥበብ ዘርፉም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አስተሳሰብ የመቅረጽ ሚናውን እንዲወጣ አቶ ተስፋሁን ጥሪ ማቅረባቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያሳያል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review