የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በሰነድ አልባ ስደተኞች በደረሰ ጥቃት ምክንያት የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስቆም 2 ሺህ ብሔራዊ ዘቦችን ወደ ሎስ አንጀለስ ልከዋል።
የአሜሪካ የድንበር አካባቢ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቶም ሆማን፣ “ሎስ አንጀለስን ይበልጥ አስተማማኝ እያደረግን ነው” ሲሉ በትናንትናው ዕለት ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም እና የተሰበሰቡ ሰዎችን ለመበተን የፀጥታ አካላት አስለቃሽ ጋዝ እና ዱላ መጠቀማቸው ተገልጿል።
በሳምንቱ በሎስ አንጀለስ በተከሰተው አለመረጋጋት፣ ዓርብ ዕለት የተያዙ 44 ሰዎችን ጨምሮ 118 ሰዎች በስደተኞች እና የጉምሩክ ደምብ ማስከበር ባለስልጣናት ታስረዋል።
የካሊፎርኒያው አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም አለመረጋጋቱን አውግዘውታል።
ይህንንም ተከትሎ ኒውሰም በትናንትናው ዕለት ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር 40 ደቂቃ የፈጀ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የአስተዳደሩ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።
ይሁንና ስለ ውይይታቸው የሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሌለ ነው የቢቢሲ ዘገባ የሚያስረዳው።
አሁን ላይ አመፁ በዋናነት የተረጋጋ ቢሆንም፣ በተቃዋሚዎች እና በሕግ አስከባሪዎች መካከል ግጭት መፈጠሩ እንደቀጠለ ተመላክቷል።
ከኋይት ሀውስ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ ሰነድ አልባ ስደተኞችን የማባረር ኃላፊነት ይዘው እየሰሩ በሚገኙ የፌደራል የስደተኞች እና የጉምሩክ ደምብ ማስከበር ባለስልጣናት ላይ እምቢተኞች ጥቃት እያደረሱ ነው” ብሏል።
ላቲኖች በመኖሪያ አካባቢያቸው ከስደተኞች እና የጉምሩክ ደምብ ማስከበር ባለስልጣናት ጋር የፈጠሩት ግጭት ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።
በታምራት ቢሻው