የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ “የወጣቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው መድረክ ከአስራ አንዱም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ የወጣቶች ተወካዮች ጋር በሀገራዊ እና ከተማ አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል ወጣቶች በአካል እና በስነልቦና ተገንብተዉ አስተማማኝ የስራ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን እና በውጤቱም ተጠቃሚ መሆናቸውን መግለፃቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም ከ1 ሺህ 400 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች መገንባታቸውን እና ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ 1.1 ሚለየን ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድሎችን እንዲያገኙ ለማስቻል በተከናወነው ስራ የበርካታዎችን ህይወት በተጨባጭ መለወጥ መቻሉን ማረጋገጣቸውን አመላክተዋል።

የከተማችን ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያ ለመዋጀት ይቻላችሁ ዘንድ ዛሬ ላይ በስነልቦና፣ በአካል ብቃት፣ በእውቀት እና በክህሎት ራሳችሁን በማዘጋጀት እያበረከታችሁ ያላችሁን አስተዋጽኦዎችን ጨምሮ በበጐ ፍቃድ አገልግሎት ለሰራችሁት የተቀደሰ ተግባር በሰላም ሰራዊት ተደራጅታችሁ የከተማችሁን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ እየሰራችሁ ላላችሁት አኩሪ ስራዎች የከተማ አስተዳደራችን በጣም ያመሰግናችኋልም ብለዋል።
ለወደፊትም የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ይበልጥ በሚያረጋግጡ አጀንዳዎች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተን እንድንሰራ ላነሳችሁልን ሀሳቦችና ጥያቄዎች የከተማ አስተዳደራችን አቅዶ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ ሲሉም አክለዋል።
ወጣቶቹ ለከተማ አስተዳደሩ ለቸሩት እውቅናም ምስጋና አቅርበዋል፡፡