የህንድ አውሮፕላን መከስከስ አደጋ ጉዳቱ ገና ትኩስ ነው። ወዳጅ ዘመድ የተፈጠረውን አምኖ ለመቀበል ከራሱ ጋር ትግል ላይ ነው። የህንድ አየርመንገድ እንዳሳወቀው አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩ 242 ሰዎች አንድ ሰው ብቻ ነው ነብስህ ትትረፍ የተባለው።
ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች መሃል አሁን ላይ የሚሰሙ ታሪኮች ሀዘንን የሚያበረቱ ናቸው። በተለይ ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ኑሮአቸውን ለንደን ለማድረግ ይጓዙ የነበሩ ባል እና ሚስት ታሪክ በሃዘን ያቆረፍዳል። ኮሚ ቪአስ ስራዋን በህንድ ያደረገች ዶክተር ናት። ባለቤቷ ፕራቲክ ጆሺ ደግሞ በስፍትዌር ኢንጂነሪንግ በለንደን ይሰራል።
የባል እና ሚስት የሁል ጊዜ ምኞት ከልጆቻቸው ጋር በጋራ የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። ሁል ጊዜ ሃሳቡን ቢያነሱትም ነገሮች ቀና ሆነው አንድ ላይ መሆን አልቻሉም። ከዚህ በላይ መጠበቅ ያቃተው ፕራቲክ ጆሺ ባለቤቱን እና ሦስቱን ልጆች ወደ ለንደን ለመውስድ ቆረጠ። ባለቤቱም በሃሳቡ ተስማምታ ስራዋን አቆመች።
በረራቸውንም ለማድረግ የህንዱ አሕመዳባድ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኙ። በመጨረሻም አንድ ላይ ለመሆን በመቃረባቸው ደስታቸው ልዩ ሆኗል። ትኬት የቆረጡበት የበረራ ቁጥር AI171 አውሮፕላን ሲገቡም በፈገግታ ተሞልተው ነው። ሁሉንም ያካተተ ማስታወሻ ፎቶ ተነስተው ለዘመድ ላኩ። ፈገግታቸው ሳይጎል አውሮፕላኑ በረራ ጀመረ።
በደስታ ብዛት እየተፍለቀለቁ የነበሩ እኚህን ቤተሰብ ግን ወዳ አሰቡት አላደረሳቸውም። ከአየር ማረፊያው ብዙም ሳይርቅ ተከሰከሰ። የቤተሰቡ አብሮ የመኖር ምኞት አብሮ ወደ ፈጣሪ በመሄድ ተደመደመ። አንጀት የሚበላው ይህ ታሪክ ኤ ቢ ሲን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን እየተቀባበሉት ይገኛል።
በሸዋንግዛው ግርማ