ህዝቡ በሰከነ መንፈስ መነጋገርንና መመካከርን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ

You are currently viewing ህዝቡ በሰከነ መንፈስ መነጋገርንና መመካከርን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ

AMN – ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

ሀገራዊ ምክክር የዜጎችን የሻከረ ግንኙነትና ማንነት የሚያድስ በመሆኑ፣ ህዝቡ በሰከነ መንፈስ መነጋገርንና መመካከርን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንዳለበት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎች ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ባሉ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ላይ መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው ተከባብሮ በመነጋገር ነው፡፡

አቶ ሲሳይ ታደሰ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በኃይል ሳይሆን በምክክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በመመካከር የሚያምን በመሆኑ፣ ዜጎች ምክክርን ባህል አድርገው ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው፤ በመከባበር መግባባት እንደሚመጣና ቀጥሎም ለተለዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

መነጋገር ጠቃሚና ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተረጋጋችና የበለፀገች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ መነጋገርና መመካከር ወሳኝና መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ ኢትዮጵያ የታላላቅ ህዝቦች ሀገር በመሆኗ ችግሮች ሲፈጠሩ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመመካከር ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡

ይህም የሻከረውን ማንነት ለማደስ፣ አንድነትን ለማጠናከር፣ ለመለወጥና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ወጣት ለምለም አዳነ፤ ተከባብሮ በመነጋገር ጥላቻ ወደ ፍቅር እንደሚቀየርና ዜጎች በየትኛውም ቦታ ተዘዋውረው መስራት እንደሚችሉ አንስታለች፡፡

ሰዎች ቅሬታ ሲኖራቸው ነፍጥ ይዘው ወደ ጫካ ከመግባት ይልቅ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባህልን ቢያዳብሩ መልካም መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ዘላለም ከበደ ናቸው፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ወ/ሮ ጌጤነሽ ሰውመሆን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዳሉ በመጥቀስ፣ በልዩነቶች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በቅን ልቦና ሀገርን በማስቀደም ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በኢትዮጵያ ያልተፈቱ ጉዳዮች እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ለሀገር እድገትም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በመግለጽ፣ የምክክሩ ተሳታፊዎች በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሳስበዋል፡፡

በሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review