AMN – ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትና ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው አለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) ገለጹ።
ፕ/ር አለማየሁ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሰንኮፍ የቴሌቪዥን መሰናዶ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ምክክር በባህሪው ልዩ ልዩ ሀሳቦች የሚነሱበትና በመጨረሻም ወደ ጋራ ስምምነት የሚያመራ ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኮሚሽኑ በተያዙት አጀንዳዎች ላይ ሙሉ በሙሉ መስማማት ባይቻል እንኳ፣ በከፊል መግባባት ላይ መድረስ ትልቅ ስኬት መሆኑንም አብራርተዋል።
የምክክሩ ሂደት አዲስ ባህል የተፈጠረበትና ችግሮችን በጦርነትና በኃይል ከመፍታት ይልቅ በንግግር ለመፍታት መንገድ የከፈተ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ ከቀደሙ ስህተቶች በመማር ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አክለውም ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎችን እያነሱ ከመወቃቀስ ይልቅ፣ ትኩረት መደረግ ያለበት ኢትዮጵያን እንደገና ታላቅና ገናና ማድረግ ላይ መሆን እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
እያንዳንዱ ሰው ማሰብ ያለበት ተጎዳሁ ብሎ ሳይሆን ኢትዮጵያን አንድ ላይ ሆነን ፣ ተደምረን ወደ ታላቅነቷ ስንመልሳት ልማት፣ ብልጽግና እናገኛለን፤ ከድህነትም እንወጣለን በሚለው አስተሳሰብ መሆን እንዳለበት ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም አብራርተዋል።
ያለፈው ዘመን የኃይልና የመገዳደል አስተሳሰብ አሁን ማብቃት እንዳለበት ያስገነዘቡት ፕ/ሩ፤ በንግግር የተጀመረ ሂደት ሁልጊዜም ወደ ሰላም እንደሚያመራ ገልጸዋል።
ከመቶ ዓመት በፊት የተፈጠረን ችግር ለመፍታት መቶ ዓመት ከመገዳደል፣ መቶ ዓመት መነጋገር ይሻላል ነው ያሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን ይህንን ታሪካዊ የምክክር ጉባኤና ሂደት ሊደግፉት እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በታደሰ ሽፈራሁ