በአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥና አውትሶርሲንግ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን
አዲስ አበባን በስሟና ሚናዋ ልክ ውብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከተማዋ የነዋሪዎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያስችሉ መሰረተ-ልማቶችን በመገንባትና ተገቢውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስማርት ሲቲ ለመሆን እየተጋች ትገኛለች፡፡
አዲስ አበባ “ስማርት ሲቲ” ለመሆን በምታደርገው ጥረት አንዱ እየሰራችበት ያለው ነዋሪው ወይም ተገልጋዩ ማህበረሰብ የሚያገኛቸውን የመንግስት አገልግሎቶች ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ከስማርት ሲቲ ምሰሶዎች አንዱ ከሆነው “ስማርት አስተዳደር” ጋር የሚያያዝ ሲሆን ተገቢውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተገልጋዮች ቤታቸው ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የማስቻል፣ ሰልፍን የመቀነስ፣ ከሰው ንክኪ ውጪ አገልግሎት በመስጠት ግልጽነትን የመፍጠርና ብልሹ አሰራርን የማስቀረት ዓላማ ያለው ነው፡፡
እንደ ሀገር የመንግስት አገልግሎትን ቀልጣፋ፣ ግልፅና ውጤታማ ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ የመንግስት ተቋማትን ሪፎርም በማድረግ እና የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በመጀመር አገልግሎትን ለማዘመን የሚደረገው ጥረትም ውጤት እያመጣ ሲሆን፣ ይህም ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆዩ ሁለት አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ኹነቶች በአዲስ አበባ እንዲካሄዱ ምክንያት እንደሆነ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
አንደኛው 10ኛው የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤ ሲሆን የመንግሥት ተቋማት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ተቋቁመው እየተንከባለሉ የመጡ ፈተናዎችን መፍታት እንዲችሉ ልምድ መለዋወጥና መማርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም ጉባኤ ነው፡፡
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ የመንግስት አገልግሎቶችን ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ በተሰራው ስራ አበረታች የሚባሉ ለውጦች መምጣታቸው የሚካድ ባይሆንም አሁንም የአገልግሎት አሰጣጡ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት አይቻልም፡፡ ክብር ባለው፣ በተቀላጠፈና ግልፅነት በተሞላበት መንገድ አገልግሎት መስጠት ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥና አውትሶርሲንግ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ በቅርብ ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ይገኛሉ፡፡ በ2016 በጀት ዓመት በርካታ ተገልጋዮችን የሚያስተናግዱ፣ ምልልስ የሚበዛባቸው፣ ቅሬታ የሚቀርብባቸው 16 ተቋማት ተመርጠው ሪፎርም ተደርገዋል፡፡ የአሰራር ስርዓቶችን በማሻሻልና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት፣ የቢሮዎችን አደረጃጀት በማስተካከል፣ ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎታቸውን ለማሻሻል እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው አብራርተዋል።
“ዓለም አሁን ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ያለ ቴክኖሎጂ የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል የማይታሰብ ነው፡፡” የሚሉት አቶ በቀለ፣ ብልሹ አሰራር፣ ሌብነት፣ ጉቦና የመሳሰሉ ችግሮች የሚቀረፉት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ መስጠት ሲቻል ነው። ከንክኪ ነፃ የሆነ፣ ተገልጋዩ በየትኛውም ቦታ ሆኖ በሲስተም አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡
ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ በርካታ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እየተሰጡ ነው፡፡ ለአብነትም የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ፣ ገቢዎች ቢሮ፣ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የንግድ ቢሮና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በከተማዋ ከ300 በላይ የሚሆኑ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እየተሰጡ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው እንደገለጹት፣ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለመስጠት ሲታቀድ አንደኛው ፋይዳ ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ቴክኖሎጂ በመምጣቱ ለወረቀት ይወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረት ተችሏል፡፡
ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማት በአካል ሲመጡ የሚወስድባቸው ጊዜና የሚያወጡት ገንዘብ አለ፡፡ የፋይል ፍለጋው፣ ወረፋና ሌሎችም ችግሮች ነበሩ። ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሚሰጠው አገልግሎት በርካታ ውጤቶች እየተገኙ ነው። ተገልጋዮች ጊዜና ገንዘባቸውን መቆጠብ፣ በተቀላጠፈና ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ አንዳንድ ቀናት፣ ሳምንታትና ከዚያም በላይ ይወስዱ የነበሩ አገልግሎቶች በደቂቃዎች መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ሁሉንም አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ አስደግፎ መስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ያነሱት አቶ በቀለ፣ በፌዴራል ደረጃ የመንግስትን አገልግሎት ቀልጣፋና ግልጽ ማድረግ የሚያስችል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጀምሯል፡፡ በአዲስ አበባም የተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል መስጠት የሚቻልበትን “አዲስ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት”ን ለማስጀመር ተቋም የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ተቋሙ አንድ ዋና መስሪያ ቤት ኖሮት በተለያዩ አካባቢዎች ቅርንጫፎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ወደ ማዕከሉ የሚገቡት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማት ናቸው፡፡ 13 ተቋማት እና የክፍያ ስርዓቱን የሚያሳልጡ ባንኮችና የቴሌኮም አገልግሎቶችን ጨምሮ ወደ አንድ ማዕከል እንዲገቡ በማድረግ ሰዎች ሳይጉላሉ ሁሉንም አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል መሆኑን አቶ በቀለ ያብራራሉ፡፡
በማዕከሉም የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲን፣ ገቢዎች ቢሮን፣ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮን፣ ንግድ ቢሮን፣ ስራና ክህሎት ቢሮን ጨምሮ የ13 ተቋማት አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተሳስረው አገልግሎት ይሰጣሉ።
የአዲስ መሶብ አገልግሎትን ለመጀመር ከቴክኖሎጂ ዝግጅት አኳያም ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ጉባኤን እንድታስተናግድ የተመረጠችበት አንዱ ምክንያት በከተማ የመንግስት አገልግሎትን ሪፎርም በማድረግና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የምትሰጠው አገልግሎት ለሌሎችም ተሞክሮ ይሆናል በሚል መሆኑን አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዮናስ ደምሰው በአዲስ አበባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የስማርት ሲቲ ዘርፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስታንዳርድ ዝግጅትና ሬጉላቶሪ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ የአዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር በአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶችን የመለየት፣ አገልግሎቱን የሚሰጡ አገልጋዮችን፣ የስራ ዝርዝርና የአሰራር ስርዓቶችን፣ቴክኖሎጂዎችን የመለየትና ግብአት የማሟላት እንዲሁም የግንባታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በኩል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ ሲሆን ወደ አዲስ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የሚገቡ ተቋማት አገልግሎታቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑን፣ ቴክኖሎጂዎችና መሰረተ ልማት ላይ መዘግየት እንዳይኖር እንዲሁም የደህንነት፣ ትስስርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ፍተሻ እየተደረገና ለአገልግሎት ብቁ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ስራውንም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ የተለያየ ቢሮና የዘርፍ ኃላፊዎች ክትትል እያደረጉበት እንዲሁም ኢንጂኒዬሮችና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ተካትተውበት እየተሰራ ነው፡፡ የወረፋ ማስጠበቂያ ስርዓት፣ ገፀ-ድርና ሌሎች አገልግሎቶችንም ዝግጁ የማድረግ ስራ አብሮ እየተሰራ እንደሆነ አቶ ዮናስ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በቴክኖሎጂ በመታገዝ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ በተገልጋዩ የኔትዎርክ መቆራረጥ ችግር እንደሚታይ ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ በቀለ ሲመልሱ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ሁለት ችግሮች ይታያሉ፡፡ አንደኛ ከኔትዎርክ አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት መቆራረጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ቴክኖሎጂን የመጠቀም ክህሎት ክፍተት በተገልጋዩ ብቻም ሳይሆን በአገልጋዩም ጭምር መስተዋሉ ነው፡፡ ይህንን ከህዝብ የሚነሳውን ችግር ለመፍታት የኔትዎርኮችን አቅም ለማሳደግ ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከአዲስ አበባ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ለሰራተኞችና ተገልጋዩ ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ አንዳንድ እንደ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ያሉ ተቋማት ዩቲዩብ፣ ቴሌግራምና ቲክቶክ በመክፈት ማህበረሰቡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግንዛቤውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው፡፡
በአገልግሎት አሰጣጣችን የህዝብ እርካታ ለማረጋገጥ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት አቶ በቀለ በበኩላቸው፣ ለዚህም ተገልጋዩን በክብርና በፈገግታ ከመቀበል መጀመር አለበት፡፡ ተገልጋዩ “የማገለግለው ቤተሰቤን ነው፤ ህዝብን በማገልገሌ እድለኛ ነኝ” የሚል አመለካከት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተቋማትን በአሰራርና አደረጃጀት የማዘመን፣ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠርና ሌሎች ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ