የጤና ባለሙያዎች ያቀረቡት ጥያቄ አግባብነት ያለዉ ቢሆንም የመፍትሄ መንገዱ ግን የእነሱ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ

You are currently viewing የጤና ባለሙያዎች ያቀረቡት ጥያቄ አግባብነት ያለዉ ቢሆንም የመፍትሄ መንገዱ ግን የእነሱ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ

AMN- ሰኔ 16/2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተዉጣጡ የጤና ባለሞያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጤናዉ ሴክተር የተነሱ የደሞዝ፤ የጥቅማ ጥቅም፤ የቤት እና መሰል ጥያቄዎች አግባብነት ያላቸዉ ቢሆኑም የመፍትሄ መንገዱ ግን የጤና ባለሙያዎች አለመሆኑን እና መነጠቁን ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ደሞዝ ወስደዉ የማያዉቁ ሰዎች የነዱት ጥያቄ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃኪም በሙያዉ ህዝብን የሚያገለግል እንደመሆኑ መጠን ሌላ አካል ጥያቄዉን እንዲያነሳበት መፍቀድ የለበትም ብለዋል፡፡

ሙያዊ ግዴታን ከመወጣትና ከኑሮ ጫና ጋር በተያያዘ የደሞዝና የጥቅማጥቅም ጥያቄ ማንሳት አግባብነት ያለዉ ትክክለኛ ጥያቄ ቢሆንም እንቅልፍ አጥቶ ማገልገልን የማያዉቁ ሰዎች የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ መጠየቃቸዉ አግባብነት የለዉም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ በሶስት ከፍለዉ አብራርተዋል፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄ ጤናማ ሙያተኞች፤ በቅንነት፤ በጨዋነት፤ ደክመዉ ህዝብ እያገለገሉ ችግር ጓዳቸዉ ስለገባ ለምን አንታይም ብለዉ ያነሱት ጥያቄ ነዉ ብለዋል፡፡

ሁለተኛዉ ጥያቄ የፖለቲካ ኪሳራ የገጠማቸው፤ ህዝብ ማገልገል ምን እንደሆነ የማያዉቁ፤ ብሔረ መንግስት ግንባታ ምን እንደሆነ የማያውቁ፤ ሁሉንም ጥያቄዎች ከደሞዝ ጋር የሚያያይዙ ፤ ከእለት ጉርስ ያለፈ እሳቤ የሌላቸዉ ሰዎች የጠለፉት ጥያቄ መሆኑም አብራርተዋል፡፡

ከሶስተኛው ጥያቄ ጋር በተያያዘም ከህክምና ተቋማት የአመት እረፍት በመዉሰድ፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስማቸዉን በመቀየር የስራ ማቆም አድማዉን ሲቀሰቅሱ የነበሩ መኖራቸዉንም አንስተዋል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ ይታወቃሉ ፤ በድንገት ጋዎን ለብሰዉ ሊሆን ይችላል ግን ሃኪሞች አይደሉም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸዉ፡፡

ከጋዎን ጋር በተያያዘም በርካታ ዜጎች ታክመዉ እየዳኑበት ስለሆነ ጋዎን ክብር አለዉ፤ የዚያ ጋዎን ክብር የሚረጋገጠዉ ግን ሃኪሞች ብቻ ሲለብሱት ነዉ ብለዋል፡፡

ሃኪም መሳይ ፖለቲከኞችና ማህበራዊ አንቂዎች ከለበሱት ግን ጋዎን ክብር ሊኖረዉ አይችልም ነዉ ያሉት፡፡

በዚህም ምክንያት ሁሉንም ጥያቄዎች በጅምላ ማየት አይገባም፤ ጥያቄዉን ማጥራት ያስፈልጋል ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመንግስትና የጤና ባለሙያዎች ሃለፊነት አለባቸዉ ብለዋል፡፡

ህዝባቸዉን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል የሚፈልጉና ንጹህ ልብ ያላቸዉ ሃኪሞች ከሌላዉ ጋር መታየት እንደሌለባቸዉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

አግባብነት ያለዉ ጥያቄ የሚያነሱትን እና ጋዎን ለብሰው አልባሌ ስራ የሚሰሩት መለየት እንዳለባቸው ገልጸው ጋዎን የለበሰ ሁሉ መነካት የለበትም የሚለዉ እሳቤ ግን ጥፋተኛዉን ከትክክለኛዉ ሃኪም ለመለየት ያስቸግራል ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review