በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሺም ሼቲማን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም ሚኒስትሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የችግኝ የተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
‘’በመትከል ማንሰራራት’’ በተሰኘው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ በእርግጥ ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ነው በማለት ለዚህም የወንዞቹን፣ የተራሮቹን ማንሰራራት ጠቅሰዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ማንሰራራት በሃገር ውስጥ እውቀት በልጆቿ ጥረት መሆኑ ያኮራናል ያሉት ከንቲባዋ፤ የዛሬ 7 ዓመት አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ሲያስጀምሩ ኢትዮጵያ በቢሊየኖች በደን ትሸፈናለች ብሎ ለማመን ያስቸግር ነበር ብለዋል።
በአዲስ አበባ ደረጃ የደን ሽፋን ከ2.8 በመቶ ተነስቶ 22 በመቶ ላይ መደረሱን ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ትናንትና እነዚህ ወንዞች በካይ ነበሩ ያሉት ከንቲባዋ፤ ዛሬ ውበትን በተላበሱት የወንዝ ዳርቻዎች እየተከልን ያለነው ምግባችንን ሲሆን ለነገ ስለ ሩሮ ውድነት፣ ስለድርቅ፣ ስለመራቆት ልመናን እና ተረጂነትን ስለማቆም ከመናገር ባሻገር ተግባራዊ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ነው ብለዋል።
ዛሬ የተተከሉ ወደፊት ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች ነገ የስራ እድል ይፈጥራሉ ያሉት ከንቲባዋ፤ በተጨማሪም በዙሪያው ያሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በርካታ የስራ እድል የሚፈጥሩ እንደሆኑ አመላክተዋል።
በሸክላ እና የሸማ ስራዎች የሚታወቁት እንጦጦና እና ሽሮሜዳ ታሪካቸው እንዳይረሳ፤ ከዛም ባለፈ የስራ እድል በመፍጠር መሸጋገር እንዲችል፤ በዘመነ መልክም ኤክስፖርት ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው የአፈር ጥበቃው እና የስነ ምህዳሩ ጥበቃ እና ከስራ እድል ጋር ተዋህዶ የተሰራ ነው።
አዲስ አበባ በተሟላ መልኩ በነገው እለት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃግብርን ወደ ማስጀመር እንደምትገባ የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ እንደልማዳችን ካቀድነው በላይ እናሳካለን ብለዋል።