ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በግብርና፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ አማራጮችን በመጠቀም ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።
ከሁለተኛ የምግብ ስርዓት ጉባኤ ጎን ለጎን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር አምና አልደሃክ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ጠንካራና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በውይይታቸው አንስተዋል።
የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን አቅምና እያከናወነች ያለውን ተግባር አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ቡናና የእንስሳት ውጤቶችን ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደምትልክ ገልጸው፣ ይህንን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ አማራጮች እንዳላት በመጥቀስ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶች በግብርና ማቀነባበሪያ፣ ማዳበሪያ ፋብሪካና ሌሎች ዘርፎች መሰማራት የሚችሉባቸው አማራጮች እንደሆኑ አብራርተውላቸዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር አምና አልደሃክ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶች በግብርና በኢንቨስትመንት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሚኒስትሮች በሁለቱ አገራት መካከል በግብርና፤በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ አማራጮችን ለመጠቀም ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ለመስራት ተስማምተዋል።