የባቡር አገልግሎት ቀድመን ጀምረን ወደኋላ መቅረታችን ቢያስቆጭም፣ ከራሳችን አልፈን አፍሪካን በባቡር ለማስተሳሰር በአዲስ ምዕራፍ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከምዕተ ዓመታት በፊት ለብዙ አፍሪካውያን የባቡር አገልግሎትን ያስተዋወቀው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር በኋላም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት፣ ለረጅም ዓመታት ግዙፍ ሀብቱን ይዞ ተቀብሮ የቆየ ተቋም ነበር ብለዋል።
ሀገራችን ቀድማ ጀምራ ኋላ የቀረችው መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አፍርሰው የመጀመር የመጥፎ ልማድ እስረኛ ሆና ለመቆየቷ አንዱ ማስረጃ መሆኑንም አንስተዋል።
የለውጡ መንግሥት በተከተለው አዲስ ዕይታና በወሰደው እርምጃ መሠረት የሀገር አንጡራ ሀብት የሆነው ተቋም፣ ባቡር እና የባቡር መሰረተ ልማት ከተቀበረበት ጥሻ ውስጥ ተፈንቅሎ እየወጣ ለመሆኑ በግቢው የሚታዩ ነገሮች ሁሉ በገፅታቸው እንደሚናገሩ ገልጸዋል።
የተደበቀው ሀብታችንን የመግለጥና የትናንት ወረትን ለሀገራዊ ብልፅግና የመጠቀም መርህን በማንገብ፣ በተጀመሩ ሥራዎች የትራንስፖርት፣ የወርክሾፕና የጥገና ሥራዎች በለውጥ ሀዲድ ላይ እንደሆኑም አመላክተዋል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር ያለው የድሬዳዋ ደወሌ ባቡር አገልግሎት የተበተነውን ሠራተኛ በመሰብሰብ፣ የቆሙ ባቡሮችን ጠግኖ ወደ ሥራ በማስገባት አሁን ላይ በሳምንት ሁለት ቀን አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለትራንስፖርት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን ማገናኘቱንም ጠቁመዋል።
በመጪው ዓመትም አገልግሎቱን ከሁለት ቀናት ከፍ ለማድረግ ዐቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ለስኬቱ የፌደራል መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በሁሉም መስክ ራሳችንን ለመቻል የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ አቅም አለን ሲሉም ነው የገለጹት።