የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቀጣይ ለሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላት በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላት አከባበርን በተመለከተ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በዋና መሥሪያ ቤቱ ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ወቅት በሰጡት የሥራ መመሪያ፤ የፀጥታና ደህንነት መዋቅሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ኃላፊነቱን በአግባቡ የተወጣ በመሆኑ አጠቃላይ ያለፉት ሁነቶች በመላው ሀገራችን በሰላም መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላትም በስኬት እንዲከበሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም የበዓላቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የፀጥታ ኃይሉ ከሕብረተሰቡ ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢሬቻ ባህልና እሴት ከሚፈቅደው ውጪ በማንኛውም ሁኔታ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን፣ ስለታማ፣ተተኳሽና ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዞ በዓሉ ወደ የሚከበርበት ስፍራ መምጣት በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን የበዓሉ ታዳሚዎችም ለፀጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።