የመቀሌ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ፣ማጣሪያና ማስወገጃ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ግንባታና ጥገና ሊደረግለት ነዉ

You are currently viewing የመቀሌ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ፣ማጣሪያና ማስወገጃ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት ግንባታና ጥገና ሊደረግለት ነዉ

AMN ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመቀሌ ከተማን የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ማጣሪያና ማስወገጃ የኦፕሬሽንና ጥገና ፕሮጀክት ግንባታ ከአሰር ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር የውል ስምምነት አደረገ።

ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የአሰር ኮንስትራክሽን ብዙ ልምድ እንዳለው አስታውሰው፤ የመቀሌን ህዝብ በሚሰራው ስራ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ከመቀሌ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ጋር በጋራ ሆነው የሚመለከታቸውንም በማሳተፍ የመቀሌ ህዝብ ችግር በፍጥነት ተፈቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የተቻላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

በትግራይ ክልል የመቀሌ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅአሸናፊ ዘአብርሃ (ዶ/ር) በክልሉም ሆነ በከተማው በገቡት ዉል መሠረት ሰርተዉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የአሰር ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ የማነ አብርሃ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰው የከተማ አስተዳደሩ ካገዛቸው በፍጥነትና በጥራት ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል።

ግንባታና ጥገናው ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን ግንባታዉ በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review