AMN – ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ለማላቅ የአዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታ፣ የህክምና ግብዓት አቅርቦት ተደራሽነት በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ግንባር ቀደም ስኬቶች ናቸው፡፡
በከተማዋ ከ2013 ዓ.ም እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ለጤው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን ባረመ መልኩ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድግ በተደረገው ርብርብ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል የጤና ተቋማት ግንባታ እና እድሳትን በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ፣የጤና ፓሊሲን የመከለስ፣ የጤና ባለሙያዎችን ማብቃትና ቁጥራቸውን ማሳደግ፣ የዲጂታል ጤና፣ ክትባት እና የህክምና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ቁጥጥር በከተማዋ በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶች ናቸው።
በዚህ ዓመት ሃምሌ ወር ላይ ብቻ በከተማ አስተዳደሩ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ አዲስ የተገነቡ፣ ማስፋፊያና ዕድሳት የተደረገላቸው 22 ጤና ጣቢያዎች ተመርቅ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ከሕንፃ ግንባታ ጀምሮ በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያና በባለሙያዎች የተደራጁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጤና ተቋማቱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት አንስተዋል፡፡
እንደ አዲስ ከተገነቡት እና ማስፋፊያ ከተደረገላቸው ጤና ተቋማት መካከል ኮልፌ መንዲዳ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ አስኮ አዲስ ሰፈርና ልደታ ጤና ጣቢያዎች ፣ ኮልፌ ወረዳ 2 ጤና ጣቢያ ፣ ንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ግዙፍ የማስፋፊያ ግንባታ ተደርጎለት በቅርቡ የተመረቀው በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የላቀ የሕክምና ማዕከል በከተማዋ ግንባታቸው ተጠናቅቀው ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

ማእከሉ ለታካሚዎች፣ ለአስታማሚዎች እና ለጤና ባለሙያዎች ምቹ ሁኔታም የፈጠረ ነው፡፡
አሁን ላይ ሕክምና ማዕከሉ 320 አልጋዎች እና 8 የኦፕሬሽን ክፍሎች እንዲሁም የራሱ ኦክስጂን ማምረቻ ፕላንት አለው።

ይሄም ከተማ አስተዳደሩ ለጤናው ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ ከመሆኑም ባለፈ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ለዘርፉ መሻሻል እና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡
የጤና ተቋማት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ሥራ ተደማሪ አቅም የሚፈጥር ይሆናል።

የእነዚህ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢዎች ወደ ስራ መግባት የህክምና ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ ለጤናው ዘርፍ ጉልህ አበርክቶ አለው፡፡
የጤና ተቋማቱ ቁጥራቸው እንዲጨምር ብቻ ሳይሆን ቴክኖሊጂን እንዲታጠቁ እየተደረገ ሲሆን ጤና ተቋማቱ በርካታ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ ነው፡፡
የሻምበል ምህረት