ሀምበሪቾ የቱሪዝም ፍሰት መናኸሪያ‎

You are currently viewing ሀምበሪቾ የቱሪዝም ፍሰት መናኸሪያ‎

AMN – ህዳር 22/2018 ዓ.ም

ከአዲስ አበባ ከተማ በ260 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሀምበሪቾ ተራራ አሁን ላይ የቱሪስቶች አዲስ መዳረሻ ሆኖ ብቅ ብሏል።

‎ሀምበሪቾ በኢትዮጵያ ካሉ ተራራዎች የተለየ እና ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ሰው ሰራሽ የሆነ 1‚554 ግዙፍ የመወጣጫ ደረጃዎች የተሰራለት ብቸኛው ተራራ መሆኑ ነው ።
ሀምበሪቾ ተራራ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከባህር ወለል በላይ በ3‚058 ሜትር ከፍታ ላይ ያለ የኢኮ-ቱሪዝም ስፍራ ነው ።

‎አካባቢው አረንጓዴ መልከዓ ምድር፣ ንጹህ አየር እና በሚያስደንቅ የተፈጥሮ ውበት የተሞላ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ መዳረሻ እየሆነ መጥቷል። የሀምበሪቾ ውበት ራስን ለማዳመጥ እና ተፈጥሮን ለማጣጣም ከራስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ እና ተራራ በመውጣት ለሚዝናኑ ዜጎች ተመራጭ ቦታ ነው ።


‎ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀምበሪቾ ኢኮ-ቱሪዝም ስፍራ ጽህፈት ቤት የብዝሃ ህይወት እና የአካባቢ አስጎብኚ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ደስታ እንደገለጹት፣ ስፍራው ለቱሪዝም ከመከፈቱ በፊት የአካባቢ ምሁራን ጥልቅ ጥናት ማድረጋቸውን ገልፀዋል ። ‎የተራራው ስም “ሀምበሪቾ 777” የተባለበት ምክንያት ከአካባቢው ሰባት ሰንሰለታማ ተራሮች ጋር ባለው ትስስር መሆኑንም ነው የተናገሩት ።

በእነዚህ ሰባት ተራሮች አናት ላይ ታሪካዊ ቦታዎች፣ የተፈጥሮ ምንጮች፣ ውብ ሸለቆዎች እንዲሁም ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራዎች ይገኛሉ።

‎በአጠቃላይ ስፍራው በ33 ትናንሽ ተራሮችና በ7 ሰንሰለታማ ተራሮች የተከበበ ሲሆን፣ ጎብኚዎች በተፈጥሯዊው መልክዓምድር አቀማመጥ ብቻ ተደንቀው የሚቆዩበት ስፍራ ሆኗል።

‎በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር አካባቢውን ከጎበኙ በኋላ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ይህም የአካባቢውን ተደራሽነት እና ተመራጭነት በእጅጉ አሻሽሎታል። የሀምበሪቾ ተራራ መወጣጫዎች 1554 ደረጃዎች ተራራው አናት ላይ ለመድረስ ምቹ ሆነው ስለተገነቡ ለጎብኚዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከጥሩ የመሬት ገጽታ እይታ ጋር ያጣምራሉ።


ከ300 በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችል ለአይን የሚማርክ ‎የባህላዊ የስብሰባ አዳራሽ በሰፍራው ተገንብቷል። እነዚህና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች በስፍራው ከተሠሩ በኋላ የቱሪስቶች ፍሰት በሦስት እጥፍ መጨመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

‎ቅዳሜና እሁድ (በዕረፍት ቀናት): ከ500 እስከ 600 የሚሆኑ ቱሪስቶች የሚጎበኝ ሲሆን፣ ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉት ቀናት ዝቅተኛው የጎብኝ ቁጥር ከ250-300 በሚደርስ ቱሪስቶች ይጎበኛል ፡፡

‎ሀምበሪቾ ተራራ በአሁኑ ሰዓት በማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም እየተመራ በመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ በቀጥተኛ እና በተዘዋዋሪ ገቢ ተጠቃሚነቱ እያደገ መጥቷል።
‌‎
‎ቀጥተኛ ገቢ ማለትም ከመግቢያ ክፍያ፣ ከድንኳን ኪራይ እና ከሌሎች አገልግሎቶች የሚገኝ ሲሆን፣ በአማካይ ቅዳሜና እሁድ ብቻ እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ ይገኛል ። ‎ጎብኚዎች ተራራው ላይ ለመቆየት ለሚፈልጉ ምቹ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የድንኳን ኪራይ አገልግሎት በአካባቢው ይሰጣል ።


‎አከባቢውን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ለአከባቢው ማህበረሰብ የሆቴል አገልግሎትን ጨምሮ አከባቢው ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሆኗል። ማህበረሰቡ እንደ ማር፣ እንሰት፣ ቡና፣ ወተት እና ሌሎችም የአካባቢ ምርቶችን ለቱሪስቶች በመሸጥ ተጠቃሚ ሆኗል።

‎በአጠቃላይ ሀምበሪቾ ተራራ የተፈጥሮን ውበት ታሪካዊ ትውፊትን ጠንካራ ማህበረሰባዊ ተጠቃሚነትን እና ምቹ መሰረተ ልማቶችን በማጣመር ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ አዲስ ተስፋ ሆኗል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review