AMN – ኅዳር 8/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የዘመኑ ሉዓላዊነት በምግብ ራስን በመቻልና በዲጂታል አቅም እንደሚረጋገጥ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ
ዘመናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ለመታገል የተቋቋመው “ለሕዝቦች ነፃነት!” ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ጠቅላላ ጉባዔ በሩሲያ ሞስኮ እየተካሄደ ይገኛል።
በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድንም በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
አቶ አደም በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ሉዓላዊነት፣ ለሀገራት እኩልነት፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቻርተር እና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲኖር ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት አፅንኦት ሰጥተው አረጋግጠዋል።
በዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛትን በመመከት እና የሕዝቦችን ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በማስከበር ረገድ ያላትን የቆየ ታሪካዊ ቅርስ ያስታወሱት አቶ አደም፣ በዘመናችን ሉዓላዊነት አዳዲስ ወቅታዊ ፈተናዎችን መቋቋምን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን በመቻል፣ በዲጂታል እና በመረጃ (ዳታ) አስተዳደር፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በኢኮኖሚ ብዝኃነት እና በተቋማዊ ማሻሻያዎች አማካኝነት ስትራቴጂካዊ ነፃነቷን ለማጠናከር እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
አክለውም ሀገሪቱ ሀብቷንና አቅሟን በማስተባበር ዘላቂና በራስ አቅም ላይ የተመሠረተ ልማት ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ግዙፍ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን፣ የስንዴ ልማትን፣ የከተማ ኮሪደር ልማትን እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባሻገር ውጤታማ የባለብዙ ወገን ትብብር በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የአፍሪካ ፍትሐዊ ውክልና መረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ ዓለም አቀፍ አጋርነቶች እንዲሁም ሰላምና እርቅ ለጋራ ብልጽግና መሠረት መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ላይ ያለው ተሳትፎ ከዲፕሎማሲያዊ ውክልና ባለፈ፤ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ እንዲሁም በሉዓላዊነት፣ በኒዮ-ኮሎኒያሊዝም፣ በልማት ነፃነት እና ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓትን በመገንባት ዙሪያ በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ የኢትዮጵያን አቋም ለማስረጽ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተመላክቷል።
ፓርቲው የፖለቲካ ምክክሮችን ወደ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ ትብብር ለመቀየር፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርስና ወቅታዊ የልማት ተሞክሮ ለማስተዋወቅ እንዲሁም እየተለዋወጠ ባለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ለማስከበር እንደሚሰራ ገልጿል።