የኪነ ጥበብ ጥቁምታ

You are currently viewing የኪነ ጥበብ ጥቁምታ

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የንባብ አውደ ርዕይ፣የህጻናት ፌስቲቫል፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

የንባብ ፌስቲቫል

በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች “አዲስ ሊትሬቸር ፌስቲቫል” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ዝግጅት እየተካሄደ ነው፡፡ አዲስ ሊትሬቸር ፌስቲቫል  ባሳለፍነው ማክሰኞ ተጀምሯል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የኪነ ጥበብ ፣ የውይይት እና የመጽሐፍ አውደ ርዕይ  እና ሌሎች ፕሮግራሞች እየተካሄዱ ነው፡፡ በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ የባህል ማዕከል ዝክረ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንን ጨምሮ ሌሎችም ዝግጅቶች ከ3፡00 ጀምሮ ይካሄዳሉ፡፡ በነገው እለትም የንባብ ውይይት፣ የመጽሐፍ ሽያጭ፣ ከደራሲዎች ጋር የመገናኘትና መጽሐፍ የማስፈረም ዝግጅት እንደሚኖር ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 75ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ “lgnite  Your Love For Words!” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው  አዲስ ሊትሬቸር ፌስቲቫል ከህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ስፍራዎች እየተሰናዳ ሲሆን እስከ ታህሣሥ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል፡፡

የህጻናት ዝግጅት

በዛሬው እለት ህጻናትን እያዝናና የሚያስተምር መርሃ ግብር ይካሄዳል። መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን መነሻ በማድረግ ሲሆን፤ በወመዘክር አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የአዋቂዎች ምክር፣ የህጻናት የባህል ባንድ፣የመጽሐፍ ስጦታ፣ የህጻናት ግጥምና መዝሙርን ጨምሮ ሌሎችም እያዝናኑ ቁምነገር የሚያስጨብጡ መርሃ ግብሮች ይከናወናሉ ተብሏል፡፡ ዝግጅቱ ከ3፡00 ጀምሮ እንደሚካሄድም አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡

ሥዕል

‘አብሮነት’ የሥዕል አውደርዕይ በመጪው ሰኞ ይጠናቀቃል፡፡ ሰዓሊያን በጋራ ሆነው ያሰናዱት የሥዕል አውደርዕይ አብሮነትና ህብረትን የሚያሳዩ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት ነው፡፡ የስዕል አውደርዕዩ በመጪው ሰኞ ይጠናቀቃል፡፡  በአውደርዕዩ ላይ የሥዕል ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ሰዓሊያን መካከል ብሩ ወርቁ፣ ያሬድ ወንድወሰንና ዘውዱ ገብረሚካኤል ይገኙበታል፡፡  የስዕል አውደርዕዩ መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ውስጥ ባለው በፈንደቃ የባህል ማዕከል ውስጥ እየታየ ይገኛል፡፡

ፊልም

“ፀሐይ” የተሰኘው ፊልም በትናንትናው እለት ተመረቀ፡፡ የአምሃ ድጉማ አዲስ ፊልም ትናንት ሕዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም  በአዲሱ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር አዳራሽ ተመርቋል፡፡ በቀይ ምንጣፍ ስሥነ ስርዓት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና  የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡ ፀሐይ ፊልም ዛሬ እና ነገም  በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች በታላቅ ድምቀት ይመረቃል ተብሏል።

ሙዚቃ

“አመል ነው” የተሰኘው የማኪ ኬቢ ሙዚቃ ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆነ፡፡ ከዚህ ቀደሞ (ደነገጠ፣ በሕልሜ ነው፣ አሜሪካ፣ ከረሜላ፣ እዩልኝ እና አልወድም) በተሠኙ ስራዎች  የምትታወቀው ሙዚቀኛ  ማኪ ኬቢ አሁንም “አመል ነው” ቆንጆ ሙዚቃ ሰርታለች፡፡ ሙዚቃው በትናንትናው እለት  በሆፕ ኢንተርቴይንመንት አማካኝነት ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆኗል፡፡ የሙዚቃው የዜማ ደራሲ ብስራት ሱራፌል ሲሆን ገጣሚው ፍሬዘር አበበወርቅ ነው፡፡

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሑድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ።  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ሁለት ቴአትሮች ለእይታ ይበቃሉ። ቀን 8፡30 ሰዓት ላይ 12ቱ እንግዶች እንዲሁም፣ 11፡30  ሰዓት ባሎችና ሚስቶች  ለእይታ ይበቃል፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት  ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ እንዲሁም  እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በ11፡30 ሰዓት ላይ ይታያሉ፡፡ በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር በሌሎች ቀናት ማክሰኞ 11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረቡዕ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ በ11፡30 ሰዓት ሸምጋይ እንዲሁም አርብ በተመሳሳይ ሰዓት ዴጊያ  የተሰኙ ቴአትሮች ለእይታ ይቀርባሉ፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review