የደርቢን ክብረወሰን ለመጋራት የሚንደረደረው ዎልቭስ

You are currently viewing የደርቢን ክብረወሰን ለመጋራት የሚንደረደረው ዎልቭስ

AMN ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም

የእንግሊዙ ዎልቭስ ለመጨረሻ ጊዜ ካሸነፈ 226 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶስት አሰልጣኞችን ቀያይሯል፡፡ ሁለት ስፖርቲንግ ዳይሬክተሮችን የለወጠው በዚሁ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

የሞሌኒኡ ክለብ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ 37 ግቦች ተቆጥውበታል፡፡ ዎልቭስ በሊጉ ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች በ12ቱ ተሸንፎ ሁለት አቻ ወጥቶ ምንም ጨዋታ ሳያሸንፍ በሁለት ነጥብ 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ወራጅ ቀጠና አፋፍ ላይ ከሚገኘው ኖቲንግሃም ፎረስት በ13 ነጥቦች ያንሳል፡፡ በወርቃማ ቀለማቸው የሚታወቁት ዎልቭሶች የደርቢ ካውንቲን ክብረወሰን ለመጋራት መጥፎ ጎዳና ላይ ናቸው፡፡

ዛሬ ምሽት በ15ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ይጫወታሉ፡፡ ዎልቭሶች ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፈው በ19881/82 ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን የተሸነፉበትን መጥፎ ክብረወሰን ለመጋራት አንድ ጨዋታ መሸነፍ ብቻ ይቀራቸዋል፡፡

ፈረንጆቹ ባጠናቀቁት ህዳር ወር በፉልሃም ሲሸነፉ ዬርሰን ሞስኩዌራ በራሱ ላይ ካስቆጠራት ግብ ውጭ አላስቆጠሩም፡፡ በቅርቡ ቪቶር ፔሬራን አሰናብተው ሮብ ኤድዋርድስን መሾማቸው ይታወቃል፡፡

‹‹በዚህ ዓይነት መንገድ መሞት አንፈልግም›› ያሉት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት አዲሱ አሰልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ ናቸው፡፡ በ2007/08 የውድድር ዓመት ደርቢ ካውንቲ 11 እንዲሁም ባለፈው ዓመት ሳውዛምፕተን 12 ነጥቦችን ይዘው ወደ ሻምፒዮንሺፕ የወረዱበት የፕሪምየር ሊጉ መጥፎ ክብረወሰን ነው፡፡

በ2018/19 እና በ2019/20 ሰባተኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰው ዎልቭስ ከዚያ በኋላ እየተንሸራተተ መጥቷል፡፡ ያለፉትን አምስት ዓመታት 13ኛ፣ 10ኛ፣ 13ኛ፣ 14ኛ እንዲሁም ባለፈው ዓመት 16ኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ሮብ ኤድዋርድስ በአራት ዓመታት ውስጥ የተሾሙ 5ኛው አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ባለፉት 12 ወራት ደግሞ ከጋሪ ኦኔልና ቪቶር ፔሬራ ቀጥሎ የተቀጠሩ ሶስተኛው አሰልጣኝ ናቸው፡፡

ዎልቭስ ውጤታማ ተጨዋቾችን ለቆ በቦታቸው አለመተካቱ ለውድቀቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ለደርቢ ካውንቲ ተጫውቶ ያሳለፈው ዛምቢያዊ አጥቂ ሮበርት ኢርንሾው ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡

ክለቡ እንደ ራወል ሂሚኔዝ፣ ሩበን ኔቬስ፣ አዳማ ትራኦሬ፣ ፔድሮ ኔቶ፣ ማክስ ኪልማንን፣ ኮኖር ኮዲና ዣኦ ሞቲንሆን የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ሸጦ የሚተካቸውን አላመጣም፡፡

ክለቡ በባለፈው ክረምትም ቢሆን ማቲያስ ኩኝሃን፣ ኔልሰን ሴሜዶን እና ራያን ኤቲ ኑሪን የመሳሰሉ ክዋክብትን ለቆ በቦታቸው የፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን አለማምጣቱ ዋጋ እንዳስከፈለው ተነግሯል፡፡

ደርቢ ካውንቲ በ2007/8 የውድድር ዓመት በዚህ ወቅት ስድስት ነጥቦችን ሰብስቦ ከዎልቭስ የተሻለ ነበር፡፡ እጅግ ደካማ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው ዎልቭስ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ 32 ሺ 50 ተመልካቾችን በሚይዘው ሞሊኒክስ ስታድዬሙ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት እየታገለ የሚገኘውን ማንችስተር ዩናይትድ ያስተናግዳል፡፡

ዎልቭስ አሸንፎ ደካማ ጉዞውን ለጊዜውም ቢሆን ይገታ ይሆን ወይስ ማንችስተር ዩናይትድ አሸንፎ ደረጃውን ያሻሻል ይሆን የምሽቱ ጨዋታ መልስ ይሰጠናል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review