ሊቨርፑል በሞሐመድ ሳላህ የተፈጠረውን ጭጋግ ለመግፈፍ ኢንተርን ይገጥማል

You are currently viewing ሊቨርፑል በሞሐመድ ሳላህ የተፈጠረውን ጭጋግ ለመግፈፍ ኢንተርን ይገጥማል

AMN ኅዳር 30 ቀን 2018 ዓ.ም

የሊቨርፑል ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መጥቷል። የቡድኑ ውጤት ማጣት ላይ የሞሐመድ ሳላህ አስተያየት ተጨምሮ የበለጠ ወደ ቀውስ እንዳያመራ ያሰጋል።

የ33 ዓመቱ ግብፃዊ ሦስት ተከታታይ ጨዋታ ተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጡ አላስደሰተውም።

“ቦታዬ በማንም ሊነጠቅ አይገባም ፤ በብቃቴ ያገኘሁት ነው።” ሲል ተናግሯል።

የቡድኑን ውጤት ማጣት በእርሱ ለማሳበብ እየተሞከረ እንደሆነ የተናገረው ሳላህ ለዚህም አሰልጣኙ እና ክለቡን ወቅሷል።

ለብዙሃን መገናኛ በሰጠው በዚህ ቃለምልልስ ምክንያት ከዛሬ ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

ከምንጊዜም የሊቨርፑል ምርጥ ተጫዋቾች እንደ አንዱ የሚቆጠረው ሳላህ የሰጠው አስተያየት ቡድኑን የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንዳይከተው ስጋት ተፈጥሯል።

አሰልጣኙ አርነ ስሎት ከጨዋታው በፊት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ በሳላህ ጉዳይ ከጨዋታው በኋላ ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚያወሩበት ጠቁመዋል።

ሊቨርፑል የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ ስድስተኛ ጨዋታውን ከኢንተር ሚላን ጋር በሳን ሲሮ ዛሬ ምሽት ያደርጋል።

ከአምስት ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብ የያዘው የመርሲሳይዱ ክለብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቀጥታ ከሚያልፉ ስምንት ክለቦች አንዱ ለመሆን ቀሪ ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ከወቅታዊ ብቃቱ መነሻ ግን ይህን ለማሳካት የሚከብደው ይመስላል።

በተለይ ዛሬ 12 ነጥብ ከሰበሰበው ኢንተር ሚላን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በእጅጉ ፈታኝ ይሆንበታል።

ነገር ግን የእንግሊዙ ክለብ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከኢንተር ሚላን ጋር ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፏል።

ይህ ታሪካዊ የበላይነቱ ተስፋ ይሰጠው ይሆን? ምሽት 5 ሰዓት የሚጀምረው ጨዋታ መልስ ይሰጠናል።

በሌሎች ጨዋታዎች ቼልሲ ወደ ቤርጋሞ አቅንቶ አታላንታን ይገጥማል። የእንግሊዙ ክለብ በ10 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፣ አታላንታም በ10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 10ኛ ላይ ይገኛል።

ባርሰሎና በሜዳው ካምፕ ናው ኢንትራክ ፍራንክፈርትን የሚገጥምበት ጨዋታም ዛሬ ይጠበቃል።

ፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከስላቪያ ፕራግ ፣ ሞናኮ ከጋላታሳራይ እንዲሁም ኡኑዮን ሴንት ጂልዋስ ከማርሴይ የሚያደርጉት ጨዋታ የምሽቱ መርሃግብር አካል ናቸው።

ሁሉም ጨዋታዎች ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚጀምሩ ይሆናል።

ምሽት 2:45 ባየርን ሙኒክ በሜዳው አልያንዝ አሬና ስፖርቲንግ ሊዝበንን ያስተናግዳል። ከዚህም ጨዋታ ቀደም ብሎ ምሽት 12:30 ኪራት አልማቲ ከኦሎምፒያኮስ ይጫወታሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review