በጊዜው አማረ
በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ። ከተሰናዱ ዋና ዋና ዝግጅቶች መካከል የንባብ አውደ ርእይ፣ የህጻናት ፌስቲቫል፣ የሥዕል አውደ ርዕይ ተጠቃሾች ናቸው። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
በዛሬው እለት ከደራሲ ሮማን ተወልደብርሃን ጋር የመወያየትና መጽሐፍት የማስፈረም መርሃ ግብር ይካሄዳል፡፡ ሮማን ከሰሞኑ “ዮዲታ” የተሰኘ የግለታሪክ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቷ ይታወሳል፡፡ መርሃ ግብሩ ከ8:00 ሰዓት እስከ 10:00 ሰዓት ለገሃር ተወልደ ህንፃ በሚገኘው ጃዕፈር መጽሐፍት ቤት እንደሆነ ተነግሯል። ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “Reflections” በሚል ርዕስ የመጀመሪያ የግጥም ስራዋን ለህትመት አብቅታለች፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ ደና’ደን በሚል ርዕስ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ያተኮረ መጽሐፏን ለልጆች አሳትማለች።
በሌላ የመጽሐፍት መረጃ የኢትዮጵያን የዘመናት ጥያቄን የመለሰውን “መሬት ላራሹ” አዋጅ ከማጥናት እስከ ህግ ማውጣት ተሳትፎ በነበራቸው ፕሮፌሰር ዓለምአንተ ገብረሥላሴ የተፃፈው “ትውስታዎቼ ስለመሬት ይዞታና የተለያዩ ፓለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች” የተሰኘው አዲስ መፅሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በአሜሪካን ሐገር የታተመ ሲሆን ለኢትዮጵያውያን አንባቢያን ደግሞ በዚህ ሳምንት ታትሞ ለንባብ በቅቷል:: መፅሐፉ ስምንት ምዕራፎች እና 268 ገጾች አሉት፡፡
የኪነ ጥበብ አውደ ርዕይ
በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ሲካሄድ የቆየው “አዲስ ሊትሬቸር ፌስቲቫል” የተሰኘ የንባብና ኪነ ጥበብ አውደ ርእይ በነገው እለት ይጠናቅቃል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የኪነ ጥበብ፣ የውይይት፣ የመጸሐፍ አውደ ርእይ እና ሌሎችም ፕሮግራሞች እየተካሄዱ ነው፡፡ ዛሬ እና ነገም የንባብ ውይይት፣ የመጽሐፍ ሽያጭ፣ ከደራሲዎች ጋር የመገናኘትና መጽሐፍ የማስፈረም መርሃ ግብር ተሰናድቷል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 75 ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ “lgnite Your Love For Words!” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው አዲስ ሊትሬቸር ፌስቲቫል ከህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ሲዘጋጅ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የስዕል አውደ ርዕይ
“የራስ መንገድ” የተሰኘ የስእል አውደ ርእይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ በዮሴፍ ሰቦቅሳ (ሰናይት) የቀረበው ይህ አውደ ርዕይ ታህሳስ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተከፈተ ሲሆን እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል። አውደ ርዕዩ መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ውስጥ ባለው በፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ እየታየ ይገኛል፡፡
ሙዚቃ
የአንጋፋው ሙዚቀኛ አረጋኸኝ ወራሽ ሙዚቃ በቅርቡ እንደሚለቀቅ ተገለጸ። “የዘመን እንቆቅልሽ” በተሰኘው አዲስ ነጠላ ሙዚቃ በግጥም መሰለ ጌታሁን፣ በዜማ እና ቅንብር ደግሞ አማኑኤል ይልማ ተሳትፈውበታል።
በሌላ መረጃ የለምለም ሃይለሚካኤል የመድረክ ስራዎች ለአድማጭ ተመልካች ሊደርሱ ነው፡፡ የድምጻዊቷ የተመረጡ 5 የመድረክ ስራዎች በናሆም ሪከርድ አማካኝነት ለህዝብ እንደሚደርሱ ተገልጿል፡፡
ቴአትር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና አሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ሁለት ቴአትሮች ለእይታ ይበቃሉ፡፡ ቀን 8፡30 ሰዓት ላይ 12ቱ እንግዶች እንዲሁም 11፡30 ሰዓት ባሎችና ሚስቶች ለእይታ ይበቃል፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ እንዲሁም በ11፡30 ሰዓት እምዩ ብረቷ፣ ማክሰኞች 11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረቡዕ በ11፡30 የቅርብ ሩቅ፣ ሃሙስ በ11፡30 ሰዓት ሸምጋይ እንዲሁም አርብ በተመሳሳይ ሰዓት ዴጊያ የተሰኙ ቴአትሮች በዚሁ ቴአትር ቤት ለእይታ ይቀርባሉ፡፡ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በአሉ ግርማ (ቤርሙዳ) ቴአትር ለተመልካች ይቀርባል፡፡