የአራራት-ኮተቤ-ካራ አስፋልት መንገድ የነዋሪዎችን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ የመለሰ ነው

You are currently viewing የአራራት-ኮተቤ-ካራ አስፋልት መንገድ የነዋሪዎችን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ የመለሰ ነው

AMN – ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም.

የአራራት-ኮተቤ-ካራ የአስፋልት መንገድ ሥራ የነዋሪዎችን የዓመታት የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የአራራት-ኮተቤ-ካራ የአስፋልት መንገድ ግንባታው በ2010ዓ.ም ተጀምሮ ከዓመታት በፊት ተጠናቆ ለዓገልግሎት ክፍት የተደረገው ቢሆንም እንኳን፤ የመንገዱ ዲዛይን ችግር የነበረበት በመሆኑ ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ ያስከትል እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኤ ኤም ኤን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌትነት አንዱ ሲሆኑ፣ የመንገዱ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተደጋጋሚ አደጋዎች ሲፈጠሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ሌላኛው አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ አለሙ ብርሃን የተባሉት የአከባቢው ነዋሪ መንገዱ ከላይ ሰፍቶ እየጠበበ ስለሚመጣ ለተደጋጋሚ አደጋ መንስኤ ሊሆን ችሏል ብለዋል።

ከሳምንት በፊት ህዝብና የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ፊት ለፊት ባገናኘው የየካ ክፍለ ከተማ የውይይት መድረክ ላይ ተሣታፊዎች እንደገለጹት ህዝብ ለሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ይህን መሰል መድረኮች ተመራጭ ናቸው ብለዋል።

የአራራት-ኮተቤ-ካራ መንገድ ትኩረት ይሰጠው በሚል በመድረኩ ለተነሳው የህዝብ ጥያቄም መንግስት ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ባለው ቁርጠኝነት የመፍትሔ እርምጃዎች ጀምሯል።

ከሰሞኑም ለፈጣን አውቶቢስ ተብሎ የተለየውን መስመር የማስተካከል ስራም በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ተጀምሯል።

ይህም ከነዋሪዎች ጋር ከተደረገው ውይይት በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የነዋሪዎቹን ቅሬታ ለመፍታት በማሰብ መንገዱን እንደገና የመገንባቱ ስራም ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን በበኩላቸው የሚስተዋለውን የአደጋ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ ስለመሆኑ በሚያረጋግጥ መልኩ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የአራራት-ኮተቤ-ካራ መንገድ አደጋ ያደርሳሉ ተብለው በጥናት ተለይተው እየተሰሩ ካሉት ሥፍራዎች መካከል አንዱ መሆኑን የገለጹት በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የመንገዶች ደህንነት ምህንድስና ዳይሬክተር አቶ መርጋ ናቸው፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review