የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት አጋርነት በማሳደግ በጋራ ጠቃሚ በሆኑ መስኮች ይበልጥ በቅርበት ለመስራት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ እና የሕንድ መሪዎች አጠቃላይ የሁለትዮሽ አጋርነትን የሚያጠናክሩ ውጤታማ እና ሰፊ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ለጀመረችው ሂደት ያላትን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡
በሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ግንኙነት ጸሀፊ ሱድሀካር ዳሌላ የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝትን አስመልክተው በአዲስ አበባ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋባዥነት በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያ ሲገቡ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ አጋርነትን የሚያጠናክር ውጤታማ እና ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ ግብርና፣ ታዳሽ ኃይል፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ክህሎት ልማት፣ መከላከያ፣ ማዕድን፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዲጂታል መሠረተ ልማት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማስፋት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ሕንድ ከምግብ እና ጤና ዋስትና አንጻር፣ በእርሻ ቴክኖሎጂ፣ በኦርጋኒክ (ተፈጥሯዊ) እርሻ፣ በዲጂታል ጤና እና ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያላትን የልማት ተሞክሮ ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶች ማድረጋቸውንና ከእነዚህ መካከል የጉምሩክ ትብብር፣ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚሰጥ ሥልጠና፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የዳታ ማዕከል መቋቋም እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ አጋርነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ መወሰናቸውን ጠቁመው፤ ይህም የሀገራቱን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል።
የአጋርነት ስምምነቱ በጠቃሚ መስኮች ላይ በቅርበት ለመስራት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የበለጠ እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።

በትምህርት፣ በክህሎት ማጎልበት እና በአቅም ግንባታ መስኮች ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውንም አንስተዋል።
ሕንድ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የምትሰጠው የአይሲሲአር (ICCR) የትምህርት ዕድል ቁጥር በእጥፍ እንደሚያድግ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ማስታወቃቸውንም እንዲሁ።
በተመሳሳይ፣ በጤና እንክብካቤ መስክ በተለይም በእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ በአደጋ ጊዜ ሕክምና እና በአደጋ ሕክምና መስኮች የመሳሪያ አቅርቦትና የሥልጠና ፕሮግራሞችን በማቅረብ የማህተመ ጋንዲ ሆስፒታልን አቅም በማሳደግ ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በመድኃኒት ማምረት ዘርፍ በኢትዮጵያ እያደገ በመጣው የሕንድ ኩባንያዎች ተሳትፎ መደሰታቸውን ገልጸዋል ብለዋል፡፡
ሕንድ እና ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ፣ ፍትሐዊ እና በሕግ ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓትን በማራመድ በኩል አንድ ሆነው እንደሚቆሙ ሁለቱ መሪዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ለጀመረችው ሂደት ያላትን ድጋፍ መግለጻቸውን አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡