AMN – ኅዳር 5/2019 ዓ.ም
የዜጎችን የቤት ፍላጎት መመለስ ከመደመር መንግሥት የልማት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ሲሆን፣ ለዚህም በተቀናጀና በዘላቂነት የሚተገበር አገራዊ አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል።
በዚህም መሠረት በአምስት ዓመታት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለዜጎች የማስረከብ ታላቅ አገራዊ ግብ ተቀምጧል።
ይህንን አገራዊ አቅጣጫ በተግባር ለማሳካት በአዲስ አበባም በ21 የቤት ልማት ሳይቶች 100 ሺህ ቤቶች በስፋት እየተገነቡ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 50 ሺህ ቤቶች በከተማው በጀት፣ ቀሪዎቹ 50 ሺህ ደግሞ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት እንዲሁም በቤት ልማት ማኅበራት እየተገነቡ መሆኑ ተገልጿል።
የመደመር መንግሥት የቤት ልማት አቅጣጫ የቤቶችን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ፤ በጥራት፣ በተመጣጣኝ ወጪ፣ በተቀናጀ የከተማ ልማትና በተለያዩ የፋይናንስና የአቅርቦት አማራጮች ለዜጎች የቤት ባለቤት የመሆን ዕድልን ማስፋት ላይ ያተኮረ ነው። የመንግሥትን አቅም፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና የማኅበራትን አቅም በማቀናጀት የቤት አቅርቦትን ማሳደግ የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ አካል ነው።

በትናንትናው ዕለት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቱሉ ዲምቱ የሚገኙ 33 ብሎኮችን እና በአዲስ ከተማ ቅጠል ተራ የሚገኙ 9 ብሎኮችን በመጎብኘት የግንባታ ሂደታቸውን ተመልክተዋል። ፕሮጀክቶቹ በጥሩ የአፈጻጸም ሂደት ላይ መሆናቸውን በመገምገም፣ የተያዙ ግቦችን በጊዜና በጥራት ለማሳካት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አሳስበዋል።
ለመደመር መንግሥት የቤት ልማት ግንባታ ብቻ አይደለም፤ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል፣ የቤት እጦትን መቀነስ፣ ለቤተሰቦች የነገ ተስፋና የኢኮኖሚ ዋስትና መፍጠር ጭምር ነው።
ስለሆነም የሕዝባችንን የቤት ጫና ለማቃለል የገባነውን ቃል በተግባር እስክንፈጽም ድረስ ያለ እረፍት፣ 24/7 በቁርጠኝነትና በከፍተኛ ኃላፊነት እንሰራለን ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው አስቀምጠዋል።
የዜጎች ቤት የልማት ግባችን ብቻ ሳይሆን የገባነው ቃልና የተሸከምነው አደራ ነው – የከንቲባ ጽ/ቤት
#housedevelopment#addisababa#Ethiopia