AMN – ኅዳር 5/2019 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱርክዬ አንታሊያ ከተማ ያደረጓቸው የሁለትዮሽ ውይይቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተሳትፎ እጅግ ውጤታማ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ወ/ሮ ቢልለኔ ሥዩም ገለጸዋል።
በቆይታቸውም ከቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በሌሎችም መስኮች የነበራቸውን የቆየ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መክረዋል።
ባለፈው ዓመት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ወደ ኢትዮጵያ አድርገውት የነበረውን ጉዞ በማስታወስ በወቅቱ የተደረሱ ስምምነቶችን አፈጻጸም ገምግመዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (ኮፕ-32) ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ በመሆኗ፣ ከቱርክዬ ልምድና እገዛ ለማግኘት ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም የቱርክዬ መንግስት እንደ አዘጋጅ ሀገር ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር በቁርጠኝነት እንደሚያደርግ አረጋግጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው መከፈት አስቀድሞ ከበርካታ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ የጋራ አጀንዳዎች ላይ የደረሱበትን ደረጃ የገመገሙ ሲሆን፣ ግንኙነቱን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል።
በጉባኤው መከፈቻ መድረክ ላይም መልዕክት ማስተላለፋቸውን ያስታወሱት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ፤ በዚህም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚደርስባቸው ጉዳት ትኩረት እንዲሰጣቸው ማሳሰባቸውን ገልፀዋል።

ሀገሪቱ ለኤልኒኖ ተጋላጭ በመሆኗ ለድርቅ እና ለጎርፍ አደጋዎች እየወሰደች ስላለችው ቅድመ ዝግጅት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተለይም የሜትሮሎጂ ስርዓቱን በማዘመን እና የቅድመ ትንተና ስልቶችን በመጠቀም አደጋ ከመድረሱ በፊት ሕብረተሰቡ እንዲዘጋጅ እየተደረጉ ስላሉ ሥራዎች አንስተዋል።
አደጋን ከመከላከል አኳያ አሁን ላይ ሥርዓቱ ይበልጥ እየተራቀቀ እና እየተሻሻለ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ቀውስን ለመከላከል የምትወስደው እርምጃ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ልምድ የሁሉም ሀገራት ባህል ሊሆን እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው መናጋራቸውን ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ገልፀዋል።
በበረከት ጌታቸው