ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት እያደገ የመጣውን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ያሳያል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት እያደገ የመጣውን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ያሳያል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ

AMN – ታኅሣሥ 8/2018 ዓ.ም

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት በሁለቱ ሀገሮች መካከል እያደገ የመጣውን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ማደግ ያሳያል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም፤ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት፣ የሚጋሯቸውን ዕሴቶችና ያላቸው ትስስር እየዳበረ መሄዱን አንስተዋል።

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ልዕልና የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሕንድ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋር መሆኗን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት በጋራ ተጠቃሚነት በተለያዩ ዘርፎች ያሉ አጋርነቶችን ለማስፋት ቁርጠኝነታችንን ያረጋገጠ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በቀጣይ ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ትብብር እንደሚጠናከርም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው አክለውም፤ ኢትዮጵያ በምትከተለው የመደመር ፍልስፍና በየዘርፉ አመርቂ ዕድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ እና ሕንድ ግንኙነት ከዲፕሎማሲም ባሻገር ትልቅ ትሥሥር ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የጥንት ሥልጣኔም ባለቤቶች መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ እና ሕንድ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማደጉንም አስታውቀዋል።

ለተሻለ የጋራ ነገም ሀገራቱ በይበልጥ በትብብር እንደሚሠሩ አመላክተው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝትም ይህን የጋራ ራዕይ ማከናወን እንዲቻል ያረጋግጣል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት እያደገ ብሎም እየሰፋ ለመጣው ወዳጅነትና አጋርነትም በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ምሥጋና አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review