የህንድ 15ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሺህ ዓመታት ድልድይ ዳግም ያደሰ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
ናሬንድራ ሞዲ ህንድ ነፃ ከወጣች በኋላ ተወልደው ሀገሪቱን ለመምራት የበቁ የመጀመሪያው መሪ ሲሆኑ የወጣትነት ዘመናቸውን ለአጭር ጊዜ እንደ መነኩሴ ከሀገር ሀገር በመዘዋወር ያሳለፉት ሞዲ፣ ዛሬም ድረስ ያ መንፈሳዊ ጽናት አብሯቸው ይገኛል።
ከፖለቲካው ጀርባ ረቂቅ ስሜት ያላቸው ገጣሚና ደራሲ ሲሆኑ ይህም በንግግራቸው ውስጥ የሚጠቀሟቸው ምስሌዎችና ብሂሎች ምንጭ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር የሁለቱን ሀገራት ስነ-ልቦናዊ ትስስር የፈተሸ ነበር።
“ድር ቢያብር…”፦ የኢትዮጵያን “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እና የህንድን “ልቦች ካበሩ ተራራ መግፋት ይቻላል” የሚሉ አባባሎችን በማነፃፀር፣ ትብብር የኃይል ምንጭ መሆኑን በረቀቀ መንገድ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን “የአንበሶች ምድር” በማለት የሰጡት ሙገሳና በ1.4 ቢሊዮን ህዝባቸው ስም ያቀረቡት ሰላምታ፣ በዲፕሎማሲው መድረክ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመጥን ነበር።
በጉብኝታቸው ወቅት በምክር ቤቱ ግቢ ውስጥ ችግኝ መትከላቸው በአረንጓዴው ቃል-ኪዳን እና “የእናት” ፍቅር ትልቅ ትርጉም አለው።
አንድ ቃል-ኪዳን፦ የህንድ “Ek Ped Maa Ke Naam” (አንድ ተክል ለእናታችን) እና የኢትዮጵያ “አረንጓዴ አሻራ” በአንድ መድረክ ተገናኝተዋል።
በሁለቱም ሀገራት ብሔራዊ መዝሙሮች ውስጥ “ሀገር በእናት” መመሰሏን በመጥቀስ፣ ለሀገር ያለውን ክብርና ኃላፊነት ስሜታዊ በሆነ መንገድ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።
የሞዲ ጉብኝት በደማቅ አቀባበል ብቻ ያበቃ አልነበረም። ህንድ በኢትዮጵያ የ5 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ እና ለ75 ሺህ ዜጎች ስራ በመፍጠር ቀዳሚ መሆኗን አስታውሰዋል።
ግንኙነቱን ወደ “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” በማሳደግ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሳይበር ደህንነት ዘርፎች በጋራ ለመስራት የተፈረሙት ስምምነቶች የቆይታቸው ዋና ፍሬዎች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቀበሉት “የኢትዮጵያ ታላቅ ክብር ኒሻን” የሁለቱን ሀገራት የዘመናት ወዳጅነት ማህተም ነው።
“በዓለም ጥንታዊ በሆነች ሀገር መከበር ኩራት ነው” ያሉት ሞዲ፣ የኢትዮጵያና የህንድ ግንኙነት ከጥቅም ባለፈ በክብርና በታሪክ የተሳሰረ መሆኑን በቆይታቸው ዳግም አረጋግጠዋል – የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት