ኢትዮጵያና አሜሪካ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ ትብብር ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ደረጃ ተሸጋግሯል – ኢንጅነር አይሻ መሃመድ

AMN – ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያና አሜሪካ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ ትብብር ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ደረጃ መሸጋገሩን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ገለጹ።

የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየም በይፋ ተከፍቷል።

የመክፈቻ ንግግር ያቀረቡት የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ፣ አዲስ አበባን የሲምፖዚየሙ አስተናጋጅ አድርጎ ለመምረጥ የተወሰነው ውሳኔ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል እያደገ የመጣውን የጋራ መተማመንና የስትራቴጂክ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሲምፖዚየሙ ከቴክኒካዊ ውይይቶች ባሻገር አጋርነትን የሚያጠናክር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚያጋራ እና በመላው አፍሪካ ብቁ፣ የተሳሰሩና ለወደፊቱ ዝግጁ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት የጋራ ቁርጠኝነትን የሚያጠናክር መድረክ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

እንዲሁም በትብብርና በፈጠራ አማካኝነት የዝግጁነት አቅምን ማሳደግ፣ በአፍሪካ አገራት የመከላከያ ኃይሎች መካከል የተቀናጀ አሠራርን ማጠናከር እና ለአህጉሪቱ ሰላም፣ ደህንነትና ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ የበለጠ ማጎልበት የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።

በዝግጅቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሰደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ (አፍሪኮም) ጀነራል ዳግላስ አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል አብዱራማን እስማኤልን ጨምሮ ከአርባ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮችና ሀያ ስድስት ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ ተወካዮች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review