ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን በማስፈን የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው

AMN – ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና ሰላምን በማስፈን ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) ጋር በመተባበር የምታስተናግደው የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚዬም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በመርሀ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል፣ የሀገራቱ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ታድመዋል።

የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ሰላም እና ደህንነት ያላት ቁርጠኝነት ዘመናትን የተሻገረ ነው፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና ሰላምን በማስፈን ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተሟላ የሎጅስቲክ እና ኮሙኒኬሽን ሥርዓት በማረጋገጥ ሽብርተኝነትን በመከላከልና ሰላምን በማስፈን የተሳካ ተልዕኮ ፈጽማለች ብለዋል፡፡

የተደራጀ የኮሙኒኬሽን ስርዓት ካልተደራጀ አስቸጋሪ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ለዘርፉ የሚሰጠውን ትኩረት ከዘመኑ ጋር በዋጀ መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

መድረኩ በዘመቻና ስምሪት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ዘመናዊ ስልት መቀየስ የሚያስችል ዕድል መፍጠር እንደሚያስችል መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review