AMN – ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ስትቆረቆር በደን የተሸፈነችና በንጹህ ምንጮች የተከበበች እንደነበረች ይጠቀሳል። ሆኖም ግን ፣ የከተሜነት መስፋፋት በጥናት ላይ የተመሰረተና በዕቅድ የተመራ ስላል ነበረ ደኖቿ ተጨፍጭፈው ወንዞቿም ለብክለት ተጋልጠው ቆይተዋል።

መዲናይቱ ጎስቋላነት ሌላኛው መገለጫዋ እስኪሆን ድረስ ከተፈጥሮና ከዘመናዊ የከተማ አሰራር ጋር ተራርቃ ነበር፡፡ የከተማዋ እጽዋት መመናመንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

በ2010 ዓ.ም የነበረው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋን መጠን ወደ 2.8% ዝቅ ብሎ ነበር። ይህም ማለት መዲናዋ ለአየር ንብረት መበከል የተጋለጠችና ለነዋሪዎቿ ምቹ ያልሆነች ከተማ ሆና እንደነበር የሚያመላክት ነው።

ይህን የከተማዋን ሁኔታ ለመቀየር በከተማ አስተዳደሩ የተወሰዱ የፖሊሲና የተግባር እርምጃዎች የየአዲስ አበባን የኋልዮሽ ጉዞ እየቀየረው ይገኛል።
አዲስ አበባን አረንጓዴ ለማልበስ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ90 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በከተማዋ በተዘጋጁ ፓርኮችና የመንገድ ዳርቻዎች ተተክለዋል። በመዲናዋ ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለአረንጓዴ ልማት ተከልሎ እንዲለማም እየተደረገ ይገኛል።

አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባ እንድትሆንና በለምለም አፀዶች እንድትታጀብ ለማድረግ የተከናወኑ የተቀናጁ ስራዎች ውጤት አስገኝተዋል ፤ በ2010 ዓ.ም 2.8% ብቻ የነበረው የመዲናዋ አረንጓዴ ሽፋን አሁን ላይ 24% መድረሱን የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ያመላክታል።
የአረንጓዴ ሽፋንን በማስፋት የተገኘው ውጤት አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው የአንድ ከተማ የ30 በመቶ አረንጓዴ ሽፋን መደበኛ መስፈርት ጋር እጅግ ያቀራርባታል።

የችግኞች ተከላና የፓርኮች መስፋፋት የከተማዋን የአየር ብክለትና የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። ፅዱና አረንጓዴ አካባቢ መስፋፋት ነዋሪዎች ንጹሕ አየር እንዲተነፍሱና ለአካላዊ ስፖርትና መዝናኛ ምቹ ሁኔታ በማዘጋጀት የአካልና የአእምሮ ጤናቸውን እንዲያጎለብቱ ዕድል ፈጥሯል።

የወንዝ ዳርቻዎችና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከ59 ኪሎሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውን የወንዝ ከባቢን በማጽዳት ፣ 2 ሺህ ሄክታር አረንጓዴ ሽፋን ፣ 24 የውሃ ግድቦችና ሰው ሰራሽ ሀይቆችን አካተው እንዲለሙ መደረጋቸውም የከተማዋን መልክአምድራዊ ገጽታ እየቀየረው ይገኛል።
ቀደም ሲል ለቆሻሻ ማከማቻነት ያገለግሉ የነበሩ ወንዞች ወደ ተፈጥሮአዊ ገጽታቸው እየተመለሱ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት መሆን ጀመረዋል።
የአረንጓዴ ስፍራዎች ፣ የህፃናት መጫወቻዎች እና የፖርኮች መስፋፋትም የከተማዋን ጎስቋላነት ገጽታ ከ74 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማድረግ አስችሏል።
የአረንጓዴ ልማቱ አዲስ አበባ በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ከሚጠቀሱ አስር ፅዱ ከተሞች አንዷ እንድትሆን አብቅቷታል። ይህ መሻሻልም በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የፅዳትና የዘመናዊ ከተማነት ሽልማቶችን እንድትቀዳጅ አስችሏታል።
በታደሠ ሽፈራው